top of page

ጥቅምት 18፣2017 - የጣና ሐይቅን የወረረው የእምቦጭ አረም የማስወገዱ ስራ በፌዴራሉ መንግስት ትኩረት ተነፍጎታል ተባለ

የጣና ሐይቅን የወረረው የእምቦጭ አረም መጠኑ እየጨመረ ቢመጣም የማስወገዱ ስራ በፌዴራሉ መንግስት ትኩረት ተነፍጎታል ተባለ፡፡


በአማራ ክልል ያለው ግጭትም አረሙን የማስወገድ ስራው እንዲቆም ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡


አረሙ አድማሱን በማስፋት የህዳሴ ግድብንም እያካለለ መሆኑን ደግሞ ጉዳዩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡


ታዲያ ምን ተሻለ? አረሙ የውሃ አካላትን ከማጥፋቱ በፊት ምን መደረግ አለበት ሲል ሸገር ኤፍኤም 102.1 ራዲዮ መንግስታዊውን የጣና ሃይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ልማት ኤጀንሲን ጠይቋል፡፡


አያሌው ወንዴ(ዶ/ር) የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት የእንቦጭ አረም የጣና ሐይቅ ላይ መታየት ከጀመረበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም በሰው ሃይልም በማሽንም አረሙን የማንሳት ስራ በዘመቻ ሲሰራ ቆይቷል፡፡


አረሙን ከ50,000 ሄክታር ወደ 2,000 እና 3,000 ሄክታር ማውረድ የተቻለበት ጊዜም እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡


ነገር ግን መልሶ እየበቀለ በዘንድሮ ዓመት በአካባቢው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመዝነቡ የአረሙ መጠን መጨመሩን በሪሞት ሴንሲግ ማሽን ተመልክተናል ብለዋል፡፡


ይህን ይባል እንጂ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ከጣና ሐይቅ ምን ያህል ሄክታሩ በአረሙ እንደተሸፈነ በውል እንደማይታወቅ ነግረውናል፡፡


ችግሩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የህዳሴ ግድብ ላይ እየታየ ያለው የእምቦጭ አረም በመጠን መጨመሩ ነውም ብለዋል ዶ/ር አያሌው፡፡


በተጨማሪም በጣና ዙሪያ ባሉ በሁሉም ማለትም በ36ቱም ቀበሌዎች አረሙ እንዳለ የሚያነሱት ስራ አስኪያጁ በተለይ በባህር ዳር ከተማ ወደ ሐይቁ የሚጣለው ቆሻሻ ለአረሙ ምግብ ስለሚሆነው አረሙ በባህር ዳር በኩል መጠኑ እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የእምቦጭ አረም ስርጭት በዚህ ከቀጠለ የውሃ አካላትን የማጥፋት አቅም አለው፡፡


ታዲያ ምን ተሻለ? ለምንስ ትኩረት ተነፈገው?

ምንታምር ፀጋው

Comments


bottom of page