‘’በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው የሚያለሙ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣት የህገወጥ ደላሎችን የግብይት ሰንሰለት አስቀርቷል’’ ሲል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተናገረ።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የግብይት ሰንሰለታቸውን በቀጥታ ከአምራቹ አርሶ አደር ጋር በማድረጋቸውም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም ተነግሯል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ ፕሮሞሽንና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን ''የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መምጣት ኢንቨስትመንቱን ከማነቃቃት፣ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት እና የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገርም ባለሀብቶች ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሮች በመግዛት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉ እና የህገወጥ ደላሎችን የገበያ ሰንሰለት ማስቀረቱ''ን ተናግረዋል።
መንግስት ካለፉት 4 እና 5 ዓመታት ወዲህ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲያለሙ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በማገዙ አሁን ላይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እየሆኑ ነው ሲሉም አቶ ዘመን ነግረውናል።
አቶ ዘመን አክለውም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ቢኖሩም በአካባቢው ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ ጥበቃ ስለሚደረግላቸው እስካሁን በፀጥታ ችግር ምክንያት ስራውን ያቋረጠ አንድም ባለሀብት እንደሌለም ሰምተናል።
በሌላ በኩል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሚያለሙ የሀገር ቤት ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል።
በጨረቃ ጨርቅ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፍርማሲቲካል ኢንዱስትሪ እና በሌላም የሀገር ቤት ባለሃብቶች እየተሰማሩ መሆኑን ሰምተናል።
ፍቅሩ አምባቸው
ความคิดเห็น