ጥቅምት 17 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Oct 27
- 2 min read
በቱርክ PKK የተሰኘው የኩርዶች የቀድሞ አማጺ ቡድን ታጣቂዎቹን ከቱርክ ወደ ኢራቅ ማስወጣት ጀመረ፡፡
PKK ታጣቂዎቹን ወደ ኢራቅ ማስወጣት የጀመረው ከቱርክ መንግስት ጋር በጀመረው የሰላም ሒደት መሰረት እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡

የኩርዶቹ ታጣቂ ቡድን ከእንግዲህ የትጥቅ አመፅ እርም ይሁንብኝ ያለው ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
በትጥቅ መፍታት ሒደት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
PKK ታጣቂነቱን ትቶ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ብቻ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
ቡድኑ ለወሰደው እርምጃ አስተማማኝነት የቱርክ መንግስት PKK ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ማህበርነት የሚለወጥበትን ሁኔታ እንዲያመቻችለት መጠየቁ ተሰምቷል፡፡
PKK የትጥቅ አመፅ እርም ይሁንብኝ ያለው ከ40 አመታት በኋላ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
በሱዳን የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የሰሜናዊ ዳርፉር ማዕከል የሆነችውን ኤል ሙሉ በሙሉ ይዣታለሁ አለ፡፡
ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ከተማዋን ለአመት ከ5 ወራት ከብቦ ሲያስጨንቅ መቆየቱን ዘናሽናል አስታውሷል፡፡
ኤል ፋሸር በዳርፉር ግዛት በመንግስት ጦር እጅ የምትገኝ ብቸኛዋ ከተማ ነበረች፡፡
RSF ከተማዋን በተቆጣጠርኩበት ማጥቃት በመንግስት ሀይሎች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሻለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ኤል ፋሸርን በእጁ ያስገባበትን የትናንቱን ቀን ታሪካዊ ሲል መጥራቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር አጋሮች ከተማይቱ ሙሉ በሙሉ ከእጃችን አልወጣችም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF ጦርነት ሲያካሂዱ ከ2 አመት ከመንፈቅ በላይ ሆኗቸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሹሞች የየመን ሁቲዎች በአገሪቱ ተጨማሪ 2 ባልደረቦቻችንን አሰሩብን አሉ፡፡
በየመን ሁቲዎች ከትናንት በስቲያ ተይዘው የታሰሩት የአለም የምግብ ፕሮግራም ባልደረቦች እንደሆኑ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በአገሪቱ የተባበሩት መንግስታት የስራ ሀላፊዎች ባልደረቦቻችን ወዴት እንደተወሰዱም ሆነ የት እንዳሉም አናውቅም ብለዋል፡፡
ከታሰሩት መካከል አንዷ በወሊድ ምክንያት ብርቱ የጤና እክል የገጠማት መሆኑ ታውቋል፡፡
የየመን ሁቲዎች በስለላ የጠረጠሯቸውን በርካታ የተባበሩት መንግስታት ባልደረቦችን አስረው እንደሚገኙ መረጃው አሰታውሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በባልደረቦቹ እስር እና መንገላታት የተነሳ በየመን ስራዬን ማከናወኑ አዳጋች ሆኖብኛል እያለ ነው፡፡
የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ አጋሮች እንደሆኑ ይነገራል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታይላንድን እና ካምቦዲያን የሰላም ስምምነት አፈራረሙ፡፡
ሰነዱ የተፈረመው በማሌዥያ አስተናጋጅነት ከሚካሄደው የደቡብ ምስራቅ እስያ አገሮች አካባቢያዊ ማህበር ጉባኤ በተጓዳኝ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የስምምት ፊርማው የተከናወነው በራሳቸው በአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጥያቄ መሰረት ነው ተብሏል፡፡
በምን ሚና እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም ትራምፕ እና የማሌዥያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂምም በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ተጠቅሷል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ትራምፕ ስለ ግል ሚናቸው ከተስማሚዎቹ በላይ አጉልተው እና ብዙ ጊዜ ሰጥተው ተናግረዋል ተብሏል፡፡
ሆኖም ስምምነቱ ስር የሰደደውን ለሁለቱ አገሮች የወሰን ይገባኛል ችግር ዘላቂ መፍትሄ የማስገኘቱ ነገር በእጅጉ አጠራጣሪ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
የጉዳዩ አዋቂዎች ችግሩ ካለው ውስብስብ ታሪካዊ መሰረት የተነሳ ዳግም ሊያገረሽ የሚችልበት እድል ሊፈጠር እንደሚችል አስተያየት መስጠታቸው መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments