የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከዚህ በኋላ የነዳጅ እጥረት ካለ ማደያዎች ሳይሆኑ ለማህበረሰቡ የማሳውቀው እኔ ነኝ አለ፡፡
ቢሮው በከተማዋ በየማደያዎቹ ያሰራጨውን የነዳጅ መጠን ከትናንት ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ማሳወቅ መጀመሩንም ተናግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ያሉ ማደያዎች በየወሩ መጨረሻ የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል እንዲሁም በቅርቡ በመንግስት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ ባሉት ቀናት አብዛኞቹ ማደያዎች ቤንዚል የለም ባነር በመለጠፍ ሸማቹን ሲሸኙ እንደነበረ ቢሮው አስታውሷል፡፡
እንደዚህ ዓይነት አርቴፊሻል እጥረት የሚፈጥሩትንና ህዝቡን የሚያጉላሉትን ማደያዎችን ለመቆጣጠር ቁጥጥር መጀመሩን ቢሮው ለሸገር ራዲዮ ተናግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገበያ መረጃና ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሰማ ጀማል ከዚህ በኋላ በየቀኑ በአዲስ አበባ ያሉ 126ቱም የነዳጅ ማደያዎች በየቀኑ ምን ያህል ነዳጅ እንዳላቸው በዝርዝር በመገናኛ ብዙሃን እንገልፃለን፤ ነዳጅ የሌላቸው ማደያዎች የትኞቹ እንደሆኑ እናሳውቃለን ብለውናል፡፡
የማሳወቅ ስራው በትናንትናው እለት መጀመሩን የነገሩን ሃላፊው ከ126ቱ በስራ ላይ ያሉት 22 ናቸው ከእነዚህም በትናንትናው እለት 87ቱ ቤንዚል ነበራቸው ብለዋል፡፡
ቀሪዎቹ 32ቱ ቤንዚል ያልነበራቸው ማደያዎች ከሰዓት ላይ ተሰራጭቶላቸዋል፤ በናፍጣ እና በሌሎችም በኩል ያለው ቁጥጥር እየተደረገበት መሆኑንም አቶ ሙሰማ ጠቅሰዋል፡፡
በከተማዋ የሚበዙት ቤንዚህ የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች ናቸው፣ናፍጣን የሚጠቀሙ ጥቂት ናቸው ብለዋል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments