top of page

ጥቅምት 14፣2017 - በኢትዮጵያ ከሚወለዱ ህፃናት ምን ያህሉ ይሞታሉ?

  • sheger1021fm
  • Oct 24, 2024
  • 2 min read

በኢትዮጵያ ከሚወለዱ ህፃናት ምን ያህሉ ይሞታሉ?


ከሚወልዱ እናቶችስ ሞት የሚያጋጥማቸው ምን ያህሎቹ ናቸው?


እነዚህንና ሌላውም በቁጥር ለማወቅ እየተጠኑ እንደሆነ ተነግሯል፡፡


ወትሮውንም ቢሆን በወሊድ ወቅት የሚከሰት የእናቶችና #ህፃናት_ሞት ከፍ ብሎ በሚታይባት ኢትዮጵያ አሁን ያለው ግጭትና መፈናቀል ተጨምሮበት ጥናቱ ምን ውጤት ይዞ ይመጣ ይሆን? የሚለው ተጠባቂ ሆኗል፡፡


‘’የኢትዮጵያ የስነ ህዝብና ጤና ጥናት’’ በሚል እነዚህንና ሌሎችንም ጤና ነክ ጉዳዮች በዝርዝር የሚጠኑበት ጥናት በየ5 ዓመቱ የሚካሄድ ነው፡፡


#ስታትስቲክስ አገልግሎት የሚከወነው ጥናቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተደረገው የዛሬ 5 ዓመት ነው፡፡


የዘንድሮው ደግሞ ካለፈው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከወነ ይገኛል፡፡


የጨቅላ ህፃናቱን ጉዳይ እንኳን ለማሳያነት ብናነሳ የዛሬ 5 ዓመት ከሚወለዱ 1,000 #ህፃናት በከተማ ከ97 በላዩ ወዲያውኑ ይሞታሉ፡፡


በገጠር ደግሞ 115 ገደማ ህፃናት ወዲያውኑ እንደሚሞቱ በስታትስቲክስ አገልግሎት የተከወነው ጥናት ያሳያል፡፡


ኢትዮጵያ የዛሬ 5 ዓመት ከነበረችበት አንፃር በብዙ ቦታዎች በጦርነትና ግጭቶች ምክንያት ጤና ጣቢያዎች ወድመዋል፤ አሁንም ሰላም የሌለባቸውና የእናቶች በጤና ተቋማት መውለድ ቅንጦት የሆነባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡


በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ እየተከወነ ያለው ጥናት ምን ውጤት ይዞ ይመጣ ይሆን? የሚለውን ተጠባቂ አድርጎታል፡፡


በዘንድሮው #ጥናት ምን ምን ጉዳዮች ተካትተዋል የሚለውን የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ ነግረውናል፡፡


በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ረገድ ኢትዮጵያ የነበረችበትን ደረጃ በየጊዜው እያሻሻለች ነው የሚሉት ባለሞያው አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በምን ደረጃ ላይ ነን የሚለውን ከጥናቱ እናገኛለን ብለውናል፡፡


ከውልደትና ሞት ባሻገር የቤተሰብ ምጣኔ በከተማና #ገጠር ምን መልክ እየያዘ ነው? አንድ ሰው ምን ያህል ልጆችን ይወልዳል፤ ልጆቹን ለመመጠን ምን አይነት ዘዴዎችን ይጠቀማል? የሚለውንም ማጥናት አስፈልጓል ይላሉ፡፡


ከዚህም ባሻገር የደባል ሱሶችና አደንዛዥ እፆች ስርጭት በተለይም በከተሞች አካባቢ እየሰፋ በመምጣቱ በዚህስ ምን ላይ ነን? የሚለውም የጥናቱ አካል ነው፡፡


ባሳለፍነው ሐምሌ ወር የተጀመረው የኢትዮጵያ የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት ለ5 ወራት ተካሂዶ በታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡


ጥናቱ በመላው ኢትዮጵያ በናሙና በተመረጡ 22,008 በሚጠጉ አባወራዎች ላይ የሚደረግ መሆኑንና እድሚያቸው ከ15 እስከ 49 ያሉ ሰዎች ላይ የሚደረግ መሆኑን ከሃላፊው ሰምተናል፡፡



ምንታምር ፀጋው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page