top of page

ጥቅምት 13፣2017 - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎችን አገደ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎችን አገደ፡፡


ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ባላቸው የሴትና የአካል ጉዳተኛ አባላት ብዛት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የአባላቱን ቁጥር አጋንነው ያቀረቡ እንዲሁም ከጠቅላላ ጉባኤ እና ከኦዲት ጋር በተገናኘ ችግር ያገኘሁባቸው በመሆኑ አግጃቸዋለሁ ሲል ባወጣው ደብዳቤ እወቁልኝ ብሏል፡፡


የዕግድ ውሳኔ የተሰጣባቸው ፓርቲዎች:-


1. የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ፣


2.አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ፣


3. ጌዲኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣


4. የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣


5. የገዳ ሥራዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፣


6. የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣


7.አዲስ ትውልድ ፓርቲ ይገኙበታል፣


8. የጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣


9. የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣


10. የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት እና


11. አገው ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲም የዕግድ ውሳኔ የተላለፈባቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡


በፓርቲዎቹ ላይ የተሰጠው የዕግድ ውሳኔ ውጤት፤ ቦርዱ የተለየ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ለጊዜው ፓርቲዎችን ከማናቸውም ሕጋዊ እንቅስቃሴ ታቅበው እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡


ፓርቲዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል እንደመሆናቸው በየትናውም አይነት እንቅስቃሴ ላይ እንዳይሳተፉ ቦርዱ ለጋራ ምክር ቤቱ በላከው ደብዳቤው አዟል፡፡


በዚህም ቦርዱ የሰጠውን የዕግድ ውሳኔ እስከሚያነሳ ድረስ በማናቸውም የጋራ ምክር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው ጉባኤዎች ላይ ሊገኙ እንዲሁም ሊመርጡም ሊመረጡም ወይም በተለያዩ የኮሚቴ አባልነት ሊያገለግሉ አይችሉም ብሏል ቦርዱ።


የጋራ ምክር ቤቱ የእግድ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ፓርቲዎች ከማናቸውም የምክር ቤቱ ሥራዎችም ሆነ እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈሉ ተገቢውን ሁሉ እንዲያደረግ ቦርዱ አሳስቧል፡፡


ከዚህ ቀደም ጉዳዩን አስመልክቶ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ሌላ ደብዳቤ ገዢውን የብልፅግና ፓርቲ ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእኔ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የተጋነነ የሴት እና የአካል ጉዳተኛ አባላት ቁጥር አቅርበውልኛል ፣ቁጥሩ አላሳመነኝም ብሎ ነበር፡፡


ፓርቲዎቹ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤኑትና በ7 ቀናት ውስጥ ትክክለኛውን የሴትና የአካል ጉዳተኛ አባላቶቻቸውን ቁጥር እንዲያስገቡ ካልሆነ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡


በወቅቱ ስማቸው የተዘረዘረው የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኞቹ አሁን ከታገዱት መካከል እንደሌሉም ከደብዳቤው ተመልክተናል፡፡

Commentaires


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page