top of page

ጥቅምት 10 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Oct 20
  • 2 min read

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ዳግም የአየር ድብደባዋን ፈፀመች ተባለ፡፡


የእስራኤል ጦር ዳግም የአየር ድብደባውን የቀጠለው በጋዛ ደቡባዊ ክፍል እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ለደቡባዊ ጋዛው የአየር ድብደባ እስራኤል በሐማስ ትንኮሳ ተፈፅሞብኛ የሚል ክስ ማቅረቧን ተሰምቷል፡፡


የእስራኤል ጦር በሐማስ ፀረ ታንክ ሚሳየል ተተኩሶብኛ ብሏል፡፡

ree

የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሐማስ በፊናው አንዲትም ጥይት አልተኮስኩም ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዛ ሰላም ባቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች የሰላም እቅድ ተፋላሚዎቹ በተኩስ አቁም ሰንብተዋል፡፡


ይሁንና እስራኤል እና ሐማስ በተኩስ አቁም መጣስ መካሰሳቸው ተደጋግሟል፡፡


የእስራኤል ጦር ከትናንቱ የጋዛ የአየር ድብደባ በኋላ ወደ ተኩስ አቁሙ ተመልሻለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡



የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የረጅም ጊዜ የተቃውሞ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ቀብራቸው ትናንት በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ተፈፀመ፡፡


ኦዲንጋ በ80 አመታቸው ከዚህ ለህክምና ባመሩባት ህንድ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ባለፈው ረቡዕ እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


ለራይላ ኦዲንጋ የተደረገው የአስከሬን ሽኝትም ሆነ ቀብራቸው ሙሉ መንግስታዊ ክብር የተቸረው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡


የተቃውሞ መሪው ከ12 አመታት በፊት የኬኒያ የቀውስ ወቅት የብሔራዊ አንድነት መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡


ለ5 ጊዜም ባይቀናቸውም በፕሬዘዳንታዊ እጩነት ቀርበው ነበር፡፡


በመጨረሻም ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበርነት ከተፎካከሩት እጩዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ በመረጃው ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡



አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን አስቸኳይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ፡፡


ሁለቱ አገሮች ተኩስ ለማቆም የተስማሙት በካታር ሸምጋይነት በዶሃ ባደረጉት ንግግር እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡


አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን በወሰን ተሻጋሪ ግጭት ውስጥ ሰንብተዋል፡፡


የካታር ሹሞች የሁለቱ አገሮች ባለስልጣናት የተኩስ አቁሙን ያለ አንዳች መዘግየት ስራ ላይ ለማዋል መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡


ተፋላሚዎቹ የተኩስ አቁሙን ስራ ላይ ለማዋል መቆጣጠሪያ መላ ለመፈለግ ንግግር ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡


ቀጣዩ ንግግራቸው ዘላቂ ሰላም በመፍጠር ላይ እንደሚያተኩር ተጠቅሷል፡፡


ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የ2ቱ አገሮች ውዝግብ እየተጋጋለ ሲሆን ግንኙነታቸውም በእጅጉ መደፍረሱ ይነገራል፡፡



በፈረንሳይዋ ርዕሰ ከተማ ፓሪስ የሚገኘው የሉቭራ ቤተ መዘክር ከባድ ዝርፊያ ተፈፀመበት ተባለ፡፡


ወደ ቤተ መዘክሩ የዘለቁት ሌቦች በከፍተኛ ቅርስነት ሲጠበቁ የኖሩ ውድ ጌጣ ጌጦችን ዘርፈዋል መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ጌጣ ጌጦቹ ከቅርስነታቸው አንፃር በዋጋ የማይታመኑ እንደሆኑ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሹሞች ተናግረዋል፡፡


ሌቦቹን የጌጣ ጌጦች ዝርፊያውን ከፈፀሙ በኋላ ከስፍራው በሞተር ብስክሌት መሰወራቸው ተሰምቷል፡፡


ሌቦቹ ለመያዝ የፀጥታ ሀይሎች አሰሳ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡


የዝርፊያው ሁኔታም በብርቱ እየተጣራ መሆኑ ታውቋል፡፡


በዝርፊያው ወቅት በቤተ መዘክሩ ላይ የመስታወት ሰበራ ማጋጠሙን መረጃው አስታውሷል፡፡



በኮንጎ ኪንሻሣ ካሳይ ግዛት የመጨረሻው የኢቦላ ታማሚ ተሽሎት ከሆስፒታል ወጣ፡፡


በመጪዎቹ 42 ቀናት አንድም በበሽታው የሚያዝ ሰው ካልተገኘ በዚያ ተቀስቅሶ የቆየው የኢቦላ ወረርሽኝ ማብቂያ እንደሚሆን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


በካሳይ ግዛት አዲሱ የኢቦላ ወረርሽኝ የተቀሰቀሰው ከወር በፊት ነው፡፡


ወረርሽኙ 45 ሰዎችን መግደሉን መረጃው አስታውሷል፡፡


በኮንጎ ኪንሻሣ ኢቦላ በወረርሽኝ ደረጃ ሲከሰት በ50 አመታት ጊዜ የአሁኑ 16ኛው ነው ተብሏል፡፡


እንደ ሰውነት ደም መፍሰስ ፣ ትኩሳት እና ማስመለስ ከኢቦላ ምልክቶች የተወሰኑ ናቸው፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page