top of page

ጥቅምት 1፣2017 - በመካከኛው ምስራቅ ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት ቀድሞም የነበረውን የቀይ ባህር መስመር ውጥረት ጨምሮታል

በመካከኛው ምስራቅ ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት ቀድሞም የነበረውን የቀይ ባህር መስመር ውጥረት ጨምሮታል፣ ይህም የኢትዮጵያን የወጪ ገቢ ንግድ ፈተና ውስጥ ከትቶታል ተብሏል፡፡


ይህንን ያለው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ነው፡፡


ኢትዮጵያ በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ #የወጪ_እና_የገቢ እቃዎችን በመርከቦች እያጓጓዘች ነው ያለው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከዚህ በላይ መስራት እንዳይቻል ቀደም ሲል የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት አሁን ደግሞ በእስራኤል፣ ሄዝቦላህ እና ሃማስ ዘመቻ በቀይ ባህር ላይ የሚደረግን ጉዞ አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግሯል፡፡


ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ደንጌ ቦሩ ከ90 በመቶ በላይ ጭነት የሚጓጓዝበት በ #ኢትዮ_ጅቡቲ የጉዞ መስመር ያለው የጋላፊ መንገድ መበላሸትም ሌላው ችግር መሆኑንና ከጂቡቲ መንግስት ጋር በመነጋገር የጥገና ስራው እየተከወነ መሆኑን ያነሳሉ፡፡


ሌላው በደረቅ ወደቦች የእቃዎች መዘግየት ሲፈጥር የነበረው እቃዎችን የሚያስመጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከወደቡ በቶሎ አለማንሳት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡


ለዚህም የጉምሩክ የአሰራር ሥርዓት ቀልጣፋ አለመሆን፣ በደረቅ ወደቦች ከሚራገፉ እቃዎች መጠን ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖር፣ በሃገር ውስጥ የነበረው የዶላር እጥረት ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡


#ማክሮ_ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት በሃገር ውስጥ የዶላር እጥረት የነበረ በመሆኑ አስመጪዎች እቃዎችን አስመጥተው ደረቅ ወደብ ከደረሰ በኋላ ነው፣ ኤልሲ ከፍተው ዶላር የሚጠይቁት፣ የጠየቁትን ዶላር አግኝተው እስከሚከፍሉ ድረስ እቃቸው በደረቅ ወደቦች ስለሚቆይ መዘግየቱ እንደሚፈጠር ሚኒስቴሩ ተናግሯል፡፡


ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ በሃገር ውስጥ የዶላር አቅርቦቱ ስለተሸሻለ ከዚህ ቀደም ወደቦችን ያጨናንቁ ነበሩ እቃዎች አሁን በቶሎ እተነሱ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ ነግረውናል፡፡

እነዚህና ሌሎችም ችግሮች ቢኖሩም በተቻለ መጠን ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠሁ ነው የሚለው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከዚህም ባለፈ 9,000 #ባህረኞችን አሰልጥኖ ከ6,000 በላዩን በውጭ ሃገራት በማስቀጠር በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም ለሃገሪቱ ከ39 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስገኘቱንም ይናገራል፡፡


የሎጀስቲክስ ዘርፉ ለሃገር ያለውን አበርክቶ ከፍ ለማድረግ አሰራሩን ማዘመን፣ አሁን ካለው በላይ የመንገድ፣ የደረቅ ወደብና ሌላውም ማስፋት ያስፈልጋል መባሉንም ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው



Comments


bottom of page