top of page

ጥር  9/2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

የአሜሪካ መንግስት በሱዳን ወታደራዊ መንግስት እና በአገሪቱ የጦር መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ላይ ማዕቀብ ጣለባቸው፡፡

 

የአሜሪካ መንግስት በአል ቡርሃን ላይ ማዕቀብ የጣለባቸው ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ ለሚገኘው የሱዳኑ ጦርነት መቀጠል አንዱ ተጠያቂ ናቸው ብሎ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

የዋይት ሐውስ አስተዳደር በአል ቡርሃን ላይ ማዕቀብ የጣለባቸው በጀዚራ ግዛቷ ማዕከል ዋድ ማዳኒ የሱዳን መንግስት ጦር በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሳይቀር ግድያ ፈፅሟል የመባሉን ሪፖርት መሰራጨት ተከተሎ ነው ተብሏል፡፡

 

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መንግስት በሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ሀይል RSF አዛዥ ሌተና ጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ ላይም ማዕቀብ መጣሉን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

በጦርነቱ ሒደት ሁለቱም መሪዎች የጦር ወንጀል እየፈፀሙ ነው በሚል ስማቸው በክፉ ሲነሳ ቆይቷል፡፡

 

ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኘው የሱዳኑ ጦርነት ያለ ሁነኛ መፍትሄ ከአመት ከ9 ወራት በላይ ሆኖታል፡፡


 

የዩጋንዳ ጦር ሰራዊት አዛዥ ጄኔራል ምዑዚ ኬኔሩጋባ ወደ ቀድሞው ትዊተር ወደ አሁኑ ኤክስ ማህበራዊ ድረ ገፅ ተገልጋይነታቸው ተመለሱ፡፡

 

ጄኔራል ምዑዚ ባለፈው ሳምንት የድረ ገጹ ተገልጋይነቴን ትቼ ሙሉ ትኩረቴን በወታደራዊ ሀላፊነቴ ላይ አደርጋለሁ ብለው እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡

 

ጄኔራሉ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጅ ናቸው፡፡

 

በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ በሚያኖሯቸው አወዛጋቢ ፅሁፎች በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡

 

ምዑዚ ኬኔሩጋባ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመድረክ ስሙ ቦቢ ዋይን የተሰኘውን የተቃውሞ መሪ ሮበርት ካያጉላኒን አንገቱን እቀላዋለሁ ማለታቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸው መሰንበቱ ሲነገር ነበር፡፡

 

አሁን ደግሞ የድረ ገፅ ተገልጋይነቴን ትቼዋለሁ ባሉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ መመለሳቸው እያስገረመ ነው ተብሏል፡፡

 

 

በቱርክ የተመረዘ የአልኮል መጠጥ ከጠጡት መካከል በጥቂቱ የ30 ሰዎች ሕይወት አለፈ ተባለ፡፡

 

ሌሎቹ 31 ሰዎች ደግሞ በተመረዘው የአልኮል መጠጥ የተነሳ ከፍተኛ የጤና እክል ገጥሟቸው በሆስፒታል የፅኑ ሕሙማን መከታተያ ይገኛሉ መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

በቱርክ ጓዳ ሰራሹ የአልኮል መጠጥ የሚያስከትለው የጤና ጉዳት እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡

 

በተረዘመው የአልኮል መጠጥ ምክንያት 6 ሰዎች ተይዘው መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡

 

የታሰሩት ግለሰቦች የተመረዘውን የአልኮል መጠጥ የሸጡ እና ያከፋፈሉ ናቸው መባሉ ተጠቅሷል፡፡

 

ከታሰሩት መካከል በሁለቱ ላይ በነፍሰ ግድያ ክስ እንደተመሰረተባቸው ታውቋል፡፡

 

መንግስት በጉዳዩ ላይ ምርመራ እና ክትትሉን ማበርታቱን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

የካታሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሞሐመድ እስራኤል በጎላን ኮረብታ አቅራቢያ ከያዘችው እና ከማንኛውም ወታደራዊ ተግባራት ነፃ እንዲሆን ከተከለለው ስፍራ ጦሯን እንድታስወጣ ጠየቁ፡፡

 

ስፍራው በሶሪያ ወሰን በኩል የሚገኝ ነው፡፡

 

የእስራኤል ጦር ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ የተደረገውን ስፍራ የያዘው ከወር በፊት የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድ በአማጺያን ግስጋሴ ስጋት ገብቷቸው ከአገር በሸሹበት ወቅት ነበር፡፡

 

የካታሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የእስራኤልን ድርጊት ሀላፊነት የጎደለው ሲሉ መጠራታቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

ሼክ ሞሐመድ በሶሪያዋ ርዕሰ ከተማ ደማስቆ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

 

ለጊዜው ለሶሪያ 200 ሜጋ ዋት ሐይል እናቀርባለን ፣ በሒደትም እንጨምራለን ብለዋል፡፡

 

አዲሱ የሶሪያ አስተዳደር ከአረብ እና ከሌሎችም አገሮች ጋር ግንኙነቱን እያሰመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡

 

የካታሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየት በተመለከተ ከእስራኤል በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

 

 

 

 

 

Bình luận


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page