ጥር 8፣2017 - ለህዳሴ ግድብ ከተሸጠው ቦንድ አብዛኛው ለህዝቡ ተመልሷል ተባለ
- sheger1021fm
- Jan 16
- 2 min read
ለህዳሴ ግድብ ከተሸጠው ቦንድ አብዛኛው (ከ14 ቢሊዮን ብር በላዩ) ለህዝቡ ተመልሷል ተባለ፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 14 ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለገቢ ማሰባሰቢያነት ሲውል የነበረውን ቦንድ ለግለሰቦችና ለተቋማት ሲሸጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ለአብነትም ከግድቡ ጅማሮ አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ያለውን እንኳን ብንመለከት በሃገር ውስጥ 17.4 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ ተሸጧል፣ በውጭ ሃገራት ላሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም 1.4 ቢሊዮን ብር ቦንድ መሸጡን በድምሩም 18.9 ቢሊዮን ብር መሸጡን የግድቡ ማስተባበሪያ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል፡፡
የቦንድ ሽያጩን የሚከውነው ልማት ባንክ፤ የመመለሻ ጊዜው የደረሰን ቦንድ ገንዘቡን ከነወለዱ እየመለስኩ ነው ብሏል፡፡
በ14 ዓመታት ውስጥ ከተሸጠው 19 ቢሊዮን ብር ከተጠጋው ቦንድ ከ14 ቢሊዮን ብር በላዩን ቦንዱን ለገዙት ግለሰቦችና ተቋማት ከነወለዱ መልሻለሁ ብሏል፡፡
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካፒታል ገበያ ዳይሬክተሩ አቶ ዳዊት አማረ፡፡
ህፃናት ቤተሰቦቻቸው በሚሰጧቸው ጥቂት ብሮች ከተገዛው ተቋማት እስከ ሚገዙት በሚሊዮን ብሮች የተቆጠረ ቦንድ ሁሉም በውስጥ ባለ አሰራር 5 ዓመትና ከዚያ በላይ ከቆየ መውሰድ ይቻላል ብለውናል፡፡
በየ6 ወሩ ደግሞ ወለድ ይኖረዋል፣ መውሰድ የማይፈልግ የመውሰጃ ጊዜውን ማራዘም ይችላል በዚህ መንገድ እንደየምርጫቸው እያስተናገድናቸው ነውም ብለዋል፡፡
በአንድ ወቅት እንደ ፋሽን ተቆጥሮ ይሸመት የነበረው የህዳሴ ቦንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ገዢዎቹ ተመናምነውብኛል የሚለው ልማት ባንኩ፤ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ‘’ምግቡ ተዘጋጅቶ የሚበላበትን ሳህን ለመግዛት የሚያስፈልገው ያህል ገንዘብ ብቻ’’ እንደቀረው ተናግሯል፡፡
ይህንንም ገንዘብ ለማሰባሰብ በተለይ የተቀዛቀዘው የአዲስ ቦንድ ግዢ በሃገር ውስጥም ይሁን በውጪ እንዲበረታ ተጠይቋል፡፡
የቦንድ ሽያጩ እየተቀዛቀዘ መጥቷል በተባለበት ወቅት የተቋቋሙ እስካሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ ምንም ያላዋጡ አዳዲስ የፋናንስ ተቋማት አሉ ተብሏል፡፡
እነዚህ ተቋማት ቦንድ እንዲገዙ፣ የገዙትም እንዲያድሱ፣ ገንዘብ ለመለገስ ቃል የገቡ የፋናንስ ተቋማት ቃላቸውን እንዲፈፅሙ በማድረግ የሚቀረውን ገንዘብ እንሰበስባለን ብለዋል፤ ልማት ባንክ የካፒታል ገበያ ዳይሬክተሩ አቶ ዳዊት አማረ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ለግድቡ መዋጮ ቦንድ ገዝታችሁ፤ የገዛችሁት ቦንድ 5 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነው በገዛችሁበት ቦታ እየቀረባችሁ ገንዘባችሁን ከነወለዱ መውሰድ ትችላላችሁ ብሏል፡፡
ይሁንና ለግንባታ ስራው ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ገንዘቡን ከመውሰድ ይልቅ የመውሰጃ ጊዜውን ለተጨማሪ ዓመታት ብታራዝሙት ይመረጣል ሲል ተናግሯል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5rs
Comments