ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የመጀመሪያውን ‘’ሱፐር አፕ’’ ለአገልግሎት አቀረብኩ አለ።
ባንኩ በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ የያዘ እና ዘመናዊ አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ሱፐር አፕ የተሰኘ መተግበሪያ ወደ ስራ አስገብቻለሁ ብሏል።
‘’ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ መተግበሪያ በሁሉም የስራ ዘርፎች ለተሰማሩ ደንበኞቻችን አሰተማማኝ፣ ጥራት ያለውና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት ደንበኛ-ተኮር አገልግሎት ለመስጠት ያስቀመጥነውን ራዕይ ይበልጥ ለማሳደግ ያስችለናል” ብለዋል የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ።

ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ ‘’በዲጂታል ባንኪንግ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መተግበሪያ ነው’’ የተባለ ሲሆን ‘’መተግበሪው በግል ሂሳብ እና ለተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ሆኖ ቀርቧል‘’ ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
አካውንቶችን መክፈት፣ ከአካውንት ወደ አካውንት በፍጥነት ገንዘብ ማስተላለፍ፣ እንዲሁም በገንዘብ ልውውጥ ላይ የተመሰረተ የብድር አገልግሎት መስጠትና ሌሎች አገልግሎቶችን በአንድ የያዘ መተግበሪያ ነው ተብሎለታል፡፡
በተጨማሪም የደንበኞችን ማንነትና በህይወት መኖራቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ የነበረውን ክፍተት በማስቀረት ባንኩ የተረጋገጠ የደንበኞች መረጃ እንዲኖረው ያስችላል ተብሏል።

ደንበኞች በአዲሱ ሱፐር አፕ ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ በሸሪዓህ ህግ መሰረት የቀረቡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ አስፋው ዓለሙ እንደ አማዞንና አሊባባ ነጋዴዎች ምርታቸውን በሱፐር አፑ በማቅረብ መሸጥ የሚችሉበት ዕድል ፈጥሯልም ብለዋል፡፡
የዚህ ግብይት ተጠቃሚዎች ክፍያቸውን በዳሸን ሱፐር አፕ አካውንታቸው በኩል በቀላሉ በመፈፀም መገበያየት እንደሚችሉ ተነግሯል።
ይህ ሱፐር አፕ ደንበኞች ዲጂታል ካርድ ወይም ቨርቹዋል ካርድ በማውጣት ከፕላስቲክ ካርዶች የተሻለ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኙም አማራጭ አቅርቧል በተጨማሪም ዳሸን ባንክ ሱፐር አፕ ደንበኞች በፍጥነት በኪው አር ኮድ አማካኝነት ክፍያ እንዲፈጽሙ እና ገንዘብ እንዲለዋወጡ የሚያስችል ነው፡፡
ሌላው በዚህ ሱፐር አፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቀርበው አገልግሎት ደንበኞች የግል ወጪያቸውን መምራት የሚችሉበት “በጀት” የተሰኘ አገልግሎት ሲሆን ይህ አገልግሎት ደንበኞች ለተለያዩ ዕለታዊ፣ ወርሃዊና አመታዊ ወጪዎቻው የመደቡትን የተለያየ በጀት በመከታተል ያለበትን ደረጃ ስለሚያሳውቅ የፋይናንስ አጠቃቀማቸውን በአግባቡ ለመምራት ያግዛቸዋልም ተብሏል።

ዳሸን ሱፐር አፕ ካካተታቸው አዲስ አገልግሎቶች ሌላኛው ደንበኞች በሶስት ንክኪ ብቻ (Three Click Shopping) የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶችን በፍጥነትና አመቺ በሆነ መልኩ መገብየት ያስችላል።
ዳሽን ባንክ ሱፐር አፕ የአየር ትኬት ለመቁረጥና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ በቴሌቲቪ አማካኝነት የአገር ውስጥ ፊልሞች ለመመልከት፣ የዲሴስቲቪ አገልግሎቶችን ለማግኘትና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችንም ያካተተ ነው፡፡
ለባንክ አገልግሎት ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነውና በዚህ ሱፐር አፕ የተካተተው ሌላኛው አገልግሎት “ቻት ባንኪንግ” ይሰኛል፡፡
ይህ አገልግሎት ደንበኞች በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ በስልካቸው የፅሁፍ መልዕክት በመለዋወጥ ገንዘብ በፍጥነት መላላክ እንዲችሉ ያደርጋል ይህን አገልግሎት ለመጠቀም ደግሞ ሁለቱም ገንዘብ የሚላላኩ ደንበኞች የዳሸን ሱፐር አፕ ተጠቃሚ መሆን ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments