ጥር 7፣2017 ወጋገን ባንክ ''ወጋገን ኢ-ብር'' የተሰኘ የሞባይል ዋሌት አገልግሎት አስጀመርኩ አለ
- sheger1021fm
- Jan 15
- 1 min read
አገልግሎቱ ደንበኞች ወደ ባንክ ቅርንጫፎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው በሞባይል ስልካቸውን ከፕሌይስቶር ወይም አፕ ስቶር ኢ-ብር የተሰኘ መተግበሪያ በማውረድ እንዲሁም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት በመጠቀም የዋሌት ሂሳብ መክፈት፣ ገንዘብ ማንቀሳቀስ፣ ክፍያ መፈፀም እና ሂሳብ ማስተዳደር የሚያስችል ነው ተብሎለታል።
የባንኩ የኢንተርፕራይዝ ሰርቪስስ ም/ሥራ አስፈፃሚ አቶ የኃላሸት ዘውዱ የወጋገን ኢ-ብር የሞባይል ዋሌት አገልግሎት ደንበኞች ካሉበት ሆነው በማንኛውም ጊዜ ገንዘብ ማስተላለፍ እና ክፍያ መፈፀም ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በኢ-ብር ፕላትፎርም ከብር 2 ትሪሊየን በላይ ግብይቶች መፈፀማቸውን ገልፀው ኢ-ብር ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች አካታች ባደረገ መልኩ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ እያደረገ ያለው አስተዋጾ በማስጀመሪያ ፕርግራሙ ላይ ተነስቷል።
የወጋገን ኢ-ብር የሞባይል ዋሌት አገልግሎት ከፕሌይ ስቶር ወይም አፕ ስቶር የኢ-ብር መተግበሪያውን በማውረድ ወይም ወደ *602# በመደወል ደንበኞች በቅድሚያ ወጋገን ባንክን በመምረጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ተብሏል።
የሞባይል ዋሌት አገልግሎቱ ደንበኞች የዋሌት ሂሳባቸውን ከመደበኛ የወጋገን ባንክ ሂሳብ ጋር በማስተሳሰር ወደ ዋሌት ሂሳብ ገንዘብ እንዲሁም ከዋሌት ሂሳብ ወደ ወጋገን ባንክ ሂሳብ ገንዘብ ማስተላለፍ እንደሚያስችል ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይም ከወጋገን ኢ-ብር ዋሌት ሂሳብ ወደ ሌላ ደንበኛ እና የዋሌት አገልግሎት ተጠቃሚ ላልሆኑ ግለሰቦች በኃዋላ ገንዘብ መላክ እና ባንኩ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የወኪል ባንክ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም በወጋገን ኢ-ብር ሞባይል ዋሌት አገልግሎት በመጠቀም ደንበኞች የሞባይል አየር ሰዓት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬት፣ የውሃ አገልግሎት ፣የትምህርት ቤት፣ የፈረስ ትራንስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መፈፀም እንደሚችሉ ታውቋል፡፡
ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉ ከብር 6 ቢሊዮን በላይ እንዲሁም ጠቅላላ ካፒታሉ ብር 11 ቢሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ጠቅላላ ሀብቱም 74.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ባንኩ ለሸገር በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
Comments