ጥር 7፣2017 - በኢትዮጵያ ከሚፈጠሩ እርግዝናዎች 42 በመቶው ያልተፈለገ እንደሆነ ይነገራል፡፡
- sheger1021fm
- Jan 15
- 1 min read
ከዚህ ውስጥም አብዛኛው እርግዝና የሚፈጠረው በአስገድዶ መድፈር መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ ተብሏል፡፡
ፅንሱን ለማጨናገፍም የሚኬደው መንገድ ትክክል ስላልሆነ ብዙዎቹ ሴቶች ለውስብስብ ችግር ይጋለጣሉ ከፍ ሲልም ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ቀላል የሚባል አይደለም ተብሏል፡፡
እንዲህ አይነት ጉዳዮች እና በስነተዋልዶ ጤና ላይ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስራዎችን እየሰሩ ቢሆንም አሁን እንደ ሀገር በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለው የሰላም እጦት ችግሩን እንዲጨምር አድርጎታል መባሉን ሰምተናል።
ይህንን ያለው በስነ ተዋልዶ ዙሪያ በኢትዮጵያ ለ25 ዓመታት ሲሰራ የቆየው አይፓስ የተሰኘ መንግስታዊ ያለሆነ ድርጅት ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ለስነ ተዋልዶ ጤና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍልን ለማገዝ ፕሮጀክት አሰናድቻለሁ ብሏል፡፡
ለሰባት ዓመታት ይቆያል የተባለው ይሄው ፕሮጀክት በአምስት ክልሎች ላይ የሚተገበር ሲሆን በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢ የሚኖሩ፣ በግጭት ምክንያት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን፣ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሴቶች እና ልጃገረዶችን ጨምሮ ለስነ ተዋልዶ ጤና ተጋላጭ የሆኑ እና አገልግሎቱን በቀላሉ ማግኘት የማይችሉትን እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ እንደሚተገበር የአይ ፓስ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ደመቀ ደስታ(ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በተለይ ከፍተኛ ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተሻለ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ለመስጠት ያሰበው ፕሮጀክቱ ከካናዳ መንግስት በተገኘ 1.2 ቢሊየን ብር ድጋፍ ነው።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ይሸፍናል የተባለው ከ6 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍልን ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሴቶችን በቀጥታ ተደራሽ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የተቀሩት 5.5 ሚሊየኑ ደግሞ አገልግሎቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ያገኛሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት ነው፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments