top of page

ጥር 30 2017 -የኢትዮጵያን የቤት ችግር ለመፍታት ሁለት ተቋማት በአዋጅ እንዲቋሙ ምክረ ሃሳብ ቀረበ

  • sheger1021fm
  • Feb 7
  • 2 min read

የኢትዮጵያን የቤት ችግር ለመፍታት ሁለት ተቋማት በአዋጅ እንዲቋሙ ምክረ ሃሳብ ቀረበ፡፡


በአዋጅ እንዲቋቋሙ የተጠየቁት ተቋማት ኢትዮጵያ ቤቶች ፋይናንስ ኮርፖሬሽን እና የቤቶች ፈንድ ናቸው፡፡


ሁለቱ ተቋማት እንዲቋቋሙ የተጠየቁት በሀገሪቱ ያለውን የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ለማጣጣም እንዲሁም መንግስት ለዜጎች ቤት የማቅረብ ግዴታውንም ለመወጣት ይረደዋል የተባለ ጥናት በቀረበበት ወቅት ነው።


ጥናቱን ያስጠናው የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሲሆን ያጠናው ደግሞ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ነው፡፡


በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ አሁን ያለባትን የቤት ችግር በተለይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የቤት ባለቤት ለማድረግ የቤት ፋይናንስ ስረዓት ያስፈልጋታል ተብሏል፡፡

በዚህ ስረዓት ውስጥ ደግሞ የቤት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን እና የቤት ፈንድን ማቋቋም ያስፈልጋል ሲሉ ጥናቱን ያቀረቡት በፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ሙሉጌታ ጌጡ(ዶ/ር) ነግረውናል፡፡


የቤቶች ፈንዱ አላማ ከተለያዩ ምንጮች ገንዝብ ማሰባሰብ ይሆናል የተባለ ሲሆን እንዲተዳደር የተጠቆመው  ደግሞ በቤቶች ፋይናንስ ኮርፖራሽን ይሆናል ተብሏል፡፡


በዚህም መሰረት የመንግስትም የግልም ሰራተኞች ከደመወዛቸው ሶስት በመቶ እንዲቆጥቡ የፋይናስስ እና ኢንሽራስ ተቋማት እንዲያዋጡ መንግስት በየዓመቱ ከሚመድበው የካፒታል በጀት 5 በመቶውን እንዲሁም ከሚሰበሰበው የንብረት ግብር ከ5 እስከ 10 በመቶውን ለቤት ልማት እንዲያውል ምክረ ሃሳብ ቀርቧል፡፡


ፈንዱ የሚሰበስበውን ገንዝብ ደግሞ በዝቅተኛ  ወለድ ለቤት ገንቢዎች ማበድር ይሆናል ተብሏል፡፡


የቤት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን አላማ ደግሞ ፈንዱን ማስተዳደር እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ተጠሪነቱም ለብሄራዊ ባንክ እንደሆን በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡


ከስድስት፣ አምስት በፊት የአለም ባንክ ባጠናው ጥናት በሀገሪቱ ባሉ ከተሞች  ያለውን የቤት ችግር ለመፍታት በአማካኝ በየዓመቱ 471,000 ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡


ብዙ ሀገራት ያለባቸውን የቤት እጥረት ለመፍታ ይህን መንገድ ተጉዟል ያሉት በፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ሙሉጌታ ጌጡ (ዶ/ር) ኢትዮጵያም ይህን መንግድ ብትጓዝ አሁን ያለባትን የቤት ችግር መፍታት ትችላለች ብለዋል፡፡


ለምሳሌ ናይጄርያ በየዓመቱ ከበጀቷ 10 በመቶውን ለቤት ልማት እንደምታውል የጠቆሙት ተመራማሪው ኢትዮጵያን ከካፒታል በጀቷ 5 በመቶውን ከግብር ታክስ ድገሞ ከ5 አስከ 10 በመቶውን እንድታውል በጥናታቸው አስቀምጠዋል።


አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉ ቤቶች 70 ከመቶዎች ከደረጃ በታች ናቸው የተባለ ሲሆን እነዚህ ተቋማት የሚቋቋሙ ከሆነ ለቤት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለማደሻም ይረዳል ሲሉ ሙሉጌታ ጌጡ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው

Comentários


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page