ጥር 30 2017 - ''የትኛው ሀይማኖት ነው የሰው ደም አፍስሱ የሚለው?'' የሀይማኖት አባቶች
- sheger1021fm
- Feb 7
- 1 min read
ስለ ሰላም ያልሰበክንበት መድረክ ባይኖርም በተግባር ለሰላም ስላኖርን በሀገሪቱ የሰው ደም መፍሰሱ ቀጥሏል ሲሉ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
በሀይማት ተቋማት እና በአማኞች በተለያዩ መድረኮች ስለሰላም እየተሰበከ ቢቆይም በተግባር ሰላም ባለመሰበኩ የንጹሀን ደም በየቦታው እየፈሰሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል የሀይማኖት አባቶች፡፡
በተግባር ካላዋልነው በቃል ብቻ ሰላም ሰላም ማለታችን ዋጋ የለውምም ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ 98 በመቶ ገደማ ህዝብ #ሀይማኖተኛ ነው እንላለን፣ የሀቅ አማኞች ከሆንን ታዲያ የትኛው ሀይማኖት ነው የሰው ደም አፍስሱ የሚለው? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሰላም እደፈረሰ ፍቅርና አንድነት እየላላ የሀይማት ክብርና ልዕልና እየተነካ እራሳችንን እየጎዳን ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ #ተጠጣቂዎች እኛው ነው ብለዋል፡፡
ለዚህ ሁሉ መፍትሄ ከፈጣሪ እና ከኛው ዘንድ ነው መሆኑ ልጆቻችን ተገንዘቡልን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ትጥቅ አንስተው ለሚነቀሳቀሱ ሁሉ እና ለመንግስት እባካችሁ ኑ #እንታረቅ የሚል የሰላም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀይማኖት አባቶቹ ይህንን የሰላም ጥሪ ያስተላለፉት፤ የኢትዮጵያ ሲቪል እና ሙያ ማህበራት ኮንግረስ ባሰናዳው መድረክ ላይ ነው፡፡

በሰላም ጥሪ እና በፀሎት መርገ ግብሩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ኢብራም ቱፋ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሀፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ፣ የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች እና ሌሎች ተጋባዥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል እና ሙያ ማህበራት ኮንግረስ ፕሬዝደንት ጌታሁን ሁሴን ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የፈረመችና እና ለሰላም ማስከበር ወታደሮቿን ወደ ተለያየ የዓለም ሀገር የመላክ ታሪክ ቢኖራትም በአሁኑ ወቅት ግን በሀገሪቱ ሰላም መታጣቱ የሚያሳዝን ነው ብለዋል፡፡
ኮንግረሱ፤ የተለያዩ የሲቪል እና ሙያ ማህበራትን ፌዴሬሽኖችን፣ ኮንፌዴሬሽኖችን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሕዝባዊ ማህበራትን እና የሀይማኖት ተቋማትን ያቀፈ ማህበር ሲሆን 51 ነጥብ 3 ሚሊዮን አባላትን አሉኝ ብሏል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments