ጥር 30 2017 - የህዝብ ተብለው የተቋቋሙ መገናኛ ብዙሀን በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት የዲሞክራሲ ተቋምነት ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁ ተነገረ
- sheger1021fm
- Feb 7
- 1 min read
የህዝብ ተብለው የተቋቋሙ መገናኛ ብዙሀን በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት የዲሞክራሲ ተቋምነት ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁ ተነገረ።
በህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን ወገንተኝነታቸው ለመንግስት አስፈጻሚው አካል ሆኗል የተባሉ እነዚሁ በመንግስት የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃን የጋራ መግባባት እንዳይኖርም እንቅፋት እየሆኑ ነው ተብሏል።
በመሆኑም በሀገራዊ ምክክሩ የህዝብ ሚዲያዎችን አስተዳደር በተመለከተ አጀንዳ ሆኖ መፍትሄ እንዲሰጠው ተጠይቋል።

ጥያቄውን ያቀረበው #የመገናኛ_ብዙሃን_ምክር_ቤት ነው። ምክር ቤቱ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ መፍትሔ ያሻቸዋል ያላቸውን ስድስት አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቤያለው ብሏል።
ምክር ቤቱ በላከልን መረጃ እንዳለው በሀገር አቀፍ ደረጃና በክልሎችም ተቋቁመው የሚሰሩ የህዝብ ሚዲያዎች በፖለቲካው አስተዳደር ስር በመሆናቸው ለብሄራዊ መግባባት ችግርም ምንጭ ሆነዋል ሲል የዘርፉ ምሁራን ያደረጓቸውን ጥናቶች በመጥቀስ ተናግሯል።
በተጨማሪም በመንግስት የሚተዳደሩ እነዚሁ ሚዲያዎች #የህዝብን_ሀብት በብቸኝነት በመጠቀም የሀብት ክፍፍሉን በተመለከተ የግሉን ዘርፍ ከተሳትፎ ውጪ አድርገውታል ብሏል።

ባለባቸው የአስተዳደር ክፍተት ምክንያትም የፖለቲካ አመለካከት አራማጅ ከስያሜያቸው ጀምሮም የብሄርና የአስተዳደር ክልልን መሰረት አድርገው የሚሰሩ በመሆናቸው ለብሔራዊ መግባባት እንቅፋት እየሆኑ ነው ሲል ምክር ቤቱ ጉዳዩ በሀገራዊ ምክክር የአስተዳደራቸው ሁኔታ መፍትሄ እንዲበጅለት ጠይቋል።
ለጋዜጠኞች ፈተና የሆነው መረጃን በነፃነት የማግኘት መብትም ባሉ ህግጋቶች መሰረት ተፈጸሚ እንዲሆን ሌላው አጀንዳ ሆኖ የቀረበ ነጥብ ሆኗል።
በተጨማሪም በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀም አፈና እና እንግልት ጨምሮ የተለያዩ ሚድያውን የተመለከቱ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ እንዳስረከበ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ተናግሯል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Comments