‘’በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ቢኖሩም ማን ምን እየሰራ እንደሆነ በቂ መረጃ የለኝም፤ ከዚህ በኋላ ግን አሰራሩ በዚህ መንገድ አይቀጥልም’’ ሲል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡
ተቋሙ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮችን ጠርቶ ዛሬ በካፒታል ሆቴል እየመከረ ነው፡፡
‘’በዝግጁቱ ላይ ሲነገር እንደሰማነው በኢትዮጵያዊያን ስም በሚመጣ ከፍተኛ ገንዘብ በየአካባቢው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እየተሰራ ቢሆንም ማን ምን እየሰራ እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቂ መረጃ የለውም፡፡
በዚህም ምክንያት በአንድ አካባቢ እና ወረዳ በቁጥር የበዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተመሳሳይ ስራ ሲሰሩ ይታያል፤ መረጃው ቢኖር ኖሮ በመነጋገር ማስተካከል ይቻል ነበር’’ ተብሏል፡፡
‘’የውሃና ኢንነርጂ ሚኒስቴር አሰራሩን የመቆጣጠር እና የመከታተል ሀላፊነት ያለበት በፓርላማውም የሚጠየቅ እንደመሆኑ የትኛው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ምን እየሰራ እንደሆነ ማወቅ ግድ ይለዋል’’ ተብሏል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ‘’የመቀራረብ የተሻለን ስራ ለመስራት ችግሮችንም ለመፍታት እንጂ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ቁጥጥሩን ለማበርታት የሚደረግ አይደለም’’ ብለዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ በ5 ክልሎች በ14 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ቀርቧል፡፡
የውሃና ኢነርጂ የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ አበራ እንዳሻው ባቀረቡት ፅሁፍ ‘’ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ቃል በተገባው መሰረት በተያዘላቸው ጊዜ ያለ መጠናቀቅ ችግር ታይቶባቸዋል’’ ብለዋል፡፡
ለምሳሌም በቦረና ዞን ብቻ 65 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስራ ላይ መሆናቸውን አካባቢው በእነዚሁ ድርጅቶች የተጨናነቀ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በዞኑ ያለው ንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ግን 34 በመቶ ሽፋኑ ደግሞ 13.8 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያዊያን ስም ከለጋሾች ተሰብስቦ የሚመጣው ገንዘብ ግን ከፍተኛ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
2,982 ገደማ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በስራ ላይ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን አጠቃላይ የፕሮጀክት የመደቡት በጀትም ወደ 108 ቢሊየን ብር ገደማ ነው ተብሏል፡፡
‘’ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የሚያግዝ ራሱን የቻለ ክፍል በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር ይቋቋማል’’ ተብሏል፡፡
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments