top of page

ጥር  3፣2016 - በቢሊየን ብር የተበጀተለት ፕሮጀክት አፈፃፀሙ ከ20 በመቶ በታች መሆኑ ተነገረ

በቢሊየን ብር የተበጀተለት የመጠጥ ውሃና ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት አፈፃፀሙ ከ20 በመቶ በታች መሆኑ ተነገረ።

 

ለተመረጡ አስር ወረዳዎች የመጠጥ ውሃንና ከፀሀይ ሀይል የኤሌክትሪክ ሀይል ለማቅረብ በሳኒቴሽን ዙሪያ የተጀመረው ፕሮጀትት የታሰበውን ያክል ያልተጓዘ ችግሩም የበዛ ሆኗል ተብሏል።

 

ፕሮጀክቱ እንከን የበዛው፤ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን የግንባታ ደረጃ የማያሟላና የሚበዛው ስራም ሳይንሳዊ ባልሆነ መንገድ በዘፈቀድ እየተሰራ እንደሆነም ሰምተናል።

 

እኛ ይህንን የሰማነው እንከን የበዛበት ነው፤ የተባለው የወተር ፎር ላይፍ ፕላስ ፕሮጀክት  (Water 4 Life+ Project)  የስራ አፈፃፀምን በተመለከተ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኦዲት ሪፖርት ሲያቀርብ ነው።

 

ቺልድረን ኢንቨትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (CIFF) ከተባለ ተቋም ጋር በትብብር የተጀመረውን ፕሮጀክት፣በወርልድ ቪዥን የፕሮጀክቱ ስራ ሲሰራ መቆየቱ ተነግሯል።

 

በመጀመሪያው የፕሮጀክት ምእራፍ በ8 ክልሎች አስር ወረዳዎች ሊሰራ የተያዘው እቅድ 800 ሺህ ህዝብ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ለማድረግ ነበር ተብሏል።

 

የሳኒቴሽንና ከፀሀይ ሀይል የኤሌክትሪክ ሀይልን ማቅረብም የፕሮጀክቱ አላማ እንደሆነ ተነግሯል።

 

ከውሃና ኢነርጂ በተጨማሪ የገንዘብ ሚኒስቴር፣የጤና ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴርም የፕሮግራሙ ባለቤቶች  ናቸው ተብሏል።

 



ወደ 80 ሚሊየን ዶላር ገደማ ገንዘብ የተበጀተለት ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምእራፍ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የሄደበት መንገድ ብዙ ችግር የነበረው አፈፃፀሙም ደካማ ነበር ተብሏል።

 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዝርዝር የስራ ሂደቱን በተመለከተ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ስራውን ከሚሰራው ወርልድ ቪዥን ሪፖርት የቀረበልኝ ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ብሏል።

 

ተቋሙ በራሱ መንገድ ባደረገው ማጣራትም የሚበዛው ስራ ከስምምነቱም፣በሀገር ደረጃ ከተቀመጠው መለኪያ (standard) ውጪ መሰራቱ ተረጋግጧል ተብሏል።

 

በቢሊየን ብር በተበጀተለት የወተር ፎር ላይፍ ፕላስ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምእራፍ 800 ሺህ ህዝብ የመጠጥ ውሃ ያገኛል ተብሎ ቢታሰብም በተሰራው ስራ ግን ውሃ ያገኘው ህዝብ ከ200 ሺህ ብዙም ያልበለጠ ነው ተብሏል።

 

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀምም 20 በመቶ ገደማ ብቻ መሆኑ ተነግሯል።

 

 

ቴዎድሮስ ወርቁ

 

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

 

Comments


bottom of page