የአዋሽ ባንክ 2ተኛው ምዕራፍ የ"ቀጠሌወን" የስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ሸለመ።
በፀሀይ ሀይል የምትሰራ ተሽከርካሪ የሰራው ወጣት የአንድ ሚሊዮን ብር ሽልማትና አምስት ሚሊዮን ብር ብድር ይሰጠዋል ተብሏል።
አዋሽ ባንክ ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና፣ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ሲያካሂድ የነበረውን የ2ተኛው ምዕራፍ የ''ቀጠሌወን” ውድድር የመዝጊያ ስነስርዓት በትናንትናው እለት አካሂዷል።

ትናንትና አሸናፊዎቹ የታወቁበት ሁለተኛው ምዕራፍ የቀጠሌወን ውድድር ሁሉም ተወዳዳሪዎች ቢያንስ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ ያለው መሰረታዊ የቢዝነስ ንድፈ-ሀሳብ አዘገጃጀት፣ ቢዝነስ ፕላን አቀራረፅና የተግባቦት እና ክህሎት የመሳሰሉት ወሳኝና መሰረታዊ ዕውቀቶችን ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉ ተነግሯል።
ወደ ሶስተኛ ዙር ያለፉት ምርጥ 8 ተወዳዳሪዎች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚለውጡበት ተጨማሪ ስልጠና እንደተሰጣቸው ሰምተናል፡፡
በውድድሩ ከፍተኛ ውጤት ያገኙ አምስት ተወዳዳሪዎች ከ200 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ተሸልመዋል።

በዚህ ውድድር ከ6ኛ እስከ 8ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎችም ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በውድድሩ አንደኛ የወጣው ተወዳዳሪ ያሸነፈው በፀሀይ ሀይል የምትሰራ ተሽከርካሪ በመስራቱ ሲሆን በሽልማት መልክ ከተሰጠው አንድ ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ያለማስያዣ አምስት ሚሊዮን ብር ብድር እንደሚሰጠው ተነግሯል።
Comments