top of page

ጥር 28፣2016 - ‘’የተገኘ ስኬት ባለመኖሩ መንግስት ለህዝቡ ምንም ማለት አልቻለም’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ


‘’ከታጣቂው ሸኔ ጋር በታንዛንያ ከተካሄደው ድርድር የተገኘ ስኬት ባለመኖሩ መንግስት ለህዝቡ ምንም ማለት አልቻለም’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።


ቡድኑ ''ከ5 ዓመት በፊት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ከሌሎች ሃይሎች በተለየ የተሰጠው ቃልም የለም'' ብለዋል።

ዛሬ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በነበረው ውይይት ላይ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ መንግስት ሸኔ ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር የተካሄደው ድርድር እና ድርድሩ ያልተሳካበትን ምክንያት የተመለከተ ነው።


‘’መንግስት በቀጣይ ከቡድኑ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ምን አስቧል?’’ ሲሉ ጉዳዩን ያነሱ የምክር ቤት አባል ጠይቀዋል።


''ከሸኔ ጋር ባለው ጉዳይ የሚነሳው አንዱ ጥያቄ ቡድኑ ምን ቃል ተገብቶለት ነው ከ5 ዓመት በፊት ወደ ሀገር ውስጥ የገባው? ምንስ ሳይፈጸምለት ቀርቶ ነው ወደ ግጭት ያመራው’’ የሚል እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ''ጥያቄው ግን ነገሩን በሴራ አይን ከመመልከት የመጣ ነው’’ ሲሉ አክለዋል።


መንግስት ከቡድኑ ጋር በታንዛንያ ድርድር እንደሚያካሂድ በጊዜው ለህዝቡ ይፋ ማድረጉን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘’በነበሩ ውይይቶች ግን ይህን አሳካን ብለን ለህዝቡ የምንነግረው ድምዳሜ ላይ ባለመደረሱ ምንም ማለት አልቻልንም’’ ብለዋል።


‘’ሸኔ ወደ ሀገር ውስጥ እንድመጣ የተገባልኝ ቃል ታጥፏል ብሎ ወደ ትጥቅ ትግል ገብቷል ቢባል እንኳን፤ ቆምኩለት የሚለውን ህዝብ ማገት፤ ልማት እንዳይሰራለት ማገድ እና ዘረፋ መፈጸም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም’’ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


‘’በመሃል ሆነው በሸኔም በሌሎች ሃይሎችም ላይ የማይጨበጥ ተስፋ ጥለው የሚጠብቁ አሉ’’ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።


ቡድኑ የሠላም አማራጭን እንዲከተል አሁንም የመንግስት ጥሪ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…bottom of page