ጥር 28፣2016 ‘’መንግስት አምባገነን ቢሆን ኖሮ በሀገሪቱ ይህን ያህል ስርዓት አልበኝነት አይበዛም ነበር’’ ሲሉ ጠ/ር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ
- sheger1021fm
- Feb 6, 2024
- 1 min read
‘’መንግስት አምባገነን ቢሆን ኖሮ በሀገሪቱ ይህን ያህል ስርዓት አልበኝነት አይበዛም ነበር’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
‘’ዲሞክራሲ ከሌለ ይህን ያህል ለህግ አለመገዛት ከየት መጣ?’’ ሲሉ የጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ ‘’ዲሞክራሲ በሌለባቸው ሀገራት ሰዎች በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በሌላም ሀገር ሆነው ትንፍሽ ማለት አይችሉም’’ ብለዋል፡፡
‘’ስርዓት አልበኝነት የተበራከተው ዲሞክራሲ መለማመድ፣ ነፃነትን ማስተዳደር ችግር ስለገጠመን ነው’’ ብለዋል፡፡
‘’በደርግ እና በኢህአዴግ ጊዜ ያለ ፍርድቤት ውሳኔ ሰዎች መግደል ነበር እኛ ግን እንኳን መግደል ሰዎችን ማሰር ችግር ሆኖብናል፣ የምናስበው ዲሞክራሲ ስለሆነ ነው’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‘’ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ወደ ሰላም ለማምጣት መንግስት ህግን የማስከበር ስራ እየሰራ ነው’’ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ‘’ይህም ስራ ይቀጥላል’’ ብለዋል፡፡
ህግ ማስከበር፣ ስራ ዕድል መፍጠር እና የማያግባቡ ጉዳዮች ላይ በሀገራዊ ምክክር በኩል መፍትሄ እንዲያገኙ መስራት የመንግስት ትኩረቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
መንግስት በሰላም ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘’ከዚህ ውጪ ግን አንደ መንግስትነቱ ህግ ያስከብራል፣ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ የሚባል ነገር አንሰማም፣አንቀበልም አናደርገውም ‘’ብለዋል፡፡
‘’በእያንዳንዷ ሰከንድ ለውይይት ዝግጁ የሆነ አካል ካለ ደግሞ በራችን ሀሌም ክፍት ነው’’ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
‘’እስራት በዛ፣ መንግስት የማይመስሉትን የፖለቲካ እና የሚዲያ ሰዎችን ያሳድዳል፣ ያስራል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አሁን እንዳለው ጥፋት ቢሆን ኖሮ ፓርክ ሳይሆን እስር ቤት ነበር መገንባት ያለበት’’ ብለዋል፡፡
‘’በጣም ብዙ መታሰር የሚገባቸው ሰዎች በየቀኑ ይታለፋሉ’’ ሲሉም ተሰምተዋል፡፡
‘’እስራት በዛ የተባለው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ከሆነ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አብዛኛዎችን አስተምሮ፣ አሰልጥኖ ለቋል አሁንም ይህ ይጥላል’’ ብለዋል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments