top of page

ጥር 27 2017 - እናት ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጣራና ግድግዳ ግብር በሚል በነዋሪው ላይ የጣለውን ግብር በፍርድ ቤት እንዲሻረ  አደረኩ አለ

እናት ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጣራና ግድግዳ ግብር በሚል በነዋሪው ላይ የጣለውን ግብር በፍርድ ቤት እንዲሻረ  አደረኩ አለ፡፡


ፓርቲው ይህን የተናገረው ዛሬ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ሰንጋ ተራ አካባቢ በሚገኘው መ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡


ፓርቲው የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ላይ የጣራና ግድግዳ ግብር መጣሉን አስመልክቶ በመሰረትኩት ክስ ከተማ አስተዳደሩ በሕዝቡ ላይ የተጣለው የጣራና ግድግዳ ግብር ህጋዊ አይደለም በሚል እንደተሻረ የፓርቲው ዋና ስራ አስኪያጅ ሰይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር) ተናግረዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ፅ/ቤት አጥንቶ ያቀረበውንና በአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ አማካኝነት ሚያዚያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ለሁሉም የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የተላለፈው የንብረት ግብር መመሪያ ሕግን ባልተከተለ መንገድና የከተማ አስተዳደሩ ባልተሰጠው ስልጣን ስራ ላይ ያዋለው መሆኑን ፓርቲው ተናግሮ ይህም ውሳኔ እንዲሻር ለሁለት ዓመት ያህል የፍርድ ክርክር ውሳኔው እንዲሻር አስደርጌአለሁ ብሏል፡፡

ውሳኔውን ያሳለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፌዴራል አስተዳደር ሥነ ሥረዓት ፍትሐብሔር ችሎት መሆኑን ሰምተናል፡፡


ከተማ አስተዳደሩ እናት ፓርቲ ለመሰረተው ክስ ሶስት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ሶስቱምን ሳይቀበላቸው መቅረቱን እናት ፓርቲ ተናግሯል።


የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ይግባኝ ጠይቋል ተብሏል፡፡


ፓርቲው ውሳኔው እንዲከበር ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደሚታገል ዋና ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡


ለክሱ ምክንያት ደግሞ የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ጊዜ ፕሮግራም ፅህፈት ቤት አጥንቶ ያቀረበው በአዲስ ፋይናንስ ቢሮ አማካኝነት ሚያዝያ 3/2015 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ፤ ለሁሉም የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የተላለፈው የንብረት ግብር መመሪያ ሕግን ባልተከተለ መንገድና የከተማ አስተዳደሩ የተላለፈው የንብረት ግብ ማስፈፀሚያ ህግን የተከተለ ባለመሆኑ እንደተሻረ የፓርቲው ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው ተናግረዋል፡፡


የጣሪያ እና ግድግዳ ግብር መመሪያን የከተማ አስተዳደሩ ያወጣው ባልተሰጠው ስልጣን እንደሆነ ፓርቲው ተናግሯል፡፡


ያሬድ እንዳሻው

Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page