ናንጎሎ ምቡምባ የናምቢያ አዲሱ ፕሬዘዳንት በመሆን ቃለ መሐላ መፈፀማቸው ተሰማ፡፡
ናንጎሎ ምቡምባ የናምቢያ ርዕሰ ብሔር በመሆን ቃለ መሐላ የፈፀሙት የፕሬዘዳንት ሐሔ ጊንጎብን ዜና እረፍት ካረዱ ከሰዓታት በኋላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የሐሔ ጊንጎብ ምክትል ሆነው የቆዩት ናንጎሎ ምቡምባ በአገሪቱ መጪው ምርጫ እስከሚከናወን ፕሬዘዳንት ሆነው ይቆያሉ ተብሏል፡፡
ናሚቢያውን በሐሔ ጊንጎብ ከዚህ አለም በሞት መለየት በእጅጉ ማዘናቸው ተጠቅሷል፡፡
አገሪቱ በአፍሪካ በሰላም እና መረጋጋቷ የምትታወቅ አገር ነች፡፡
ናሚቢያ በመጪው አመት ህዳር ወር ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እንደምታከናውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የሴኔጋሉ ምርጫ ጉዳይ ከወዲሁ እያራበሸ ነው ተባለ፡፡
ፕሬዘዳንት ማኪ ሳል የመጪው ምርጫ መካሄጃ በደፈናው ተራዝሟል ማለታቸው የአዲሱ ምርጫ ነክ ረብሻ መነሻ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ማኪ ሳል የምርጫ መካሄጃውን ጊዜ አራዝሜዋለሁ ያሉት የእጩዎቹ ዝርዝር እያወዛገበ ነው የሚል ምክንያት በማቅረብ ነው፡፡
ፕሬዘዳንቱ ባያራዝሙት ኖሮ ምርጫው ከ3 ሳምንታት በኋላ ይከናወን ነበር፡፡
ማኪ ሳል የምርጫውን መካሄጃ ማራዘማቸውን በመቃወም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በርዕሰ ከተማዋ ዳካር መካሄጃ ማራዘማቸውን ሰልፍ ወጥተው ውለዋል፡፡
ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውም ታውቋል፡፡
በጥቂቱ 1 የተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር መሪ ተይዘው መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡
ማኪ ሳል የምርጫውን መካሄጃ ጊዜ አራዝሜዋለሁ ቢሉም ሌላ የምርጫ ማካሄጃ ቀን አልጠቀሱም ተብሏል፡፡
የሴኔጋል ሹሞች ምርጫውን በተመለከተ ግጭት ቀስቃሽ ነው ያሉትን አንድ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ መዝጋታቸውን የፃፈው ደግሞ አናዶሉ ነው፡፡
የዋይት ሐውስ ሹሞች ባለፈው ሳምንት አርብ በኢራቅ እና ሶሪያ በሚገኙ የኢራን ደጋፊ ታጣቂዎች ላይ በአሜሪካ የተፈፀመው ድብደባ ገና ጅማሬው እንደሆነ እወቁልን አሉ፡፡
የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ስለ ድብደባው ገና ምኑ ተነካና ማለታቸውን የፃፈው ቢቢሲ ነው፡፡
ኢራን በበኩሏ አሜሪካ በኢራቅ እና ሶሪያ በሚገኙ 85 ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈፀሟን ስትራተጂያዊ ስህተት ስትል ጠርታዋለች፡፡
የፋርሳዊቱ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአሜሪካ ድብደባ በቀጠናው ውጥረት እና ፍጥጫውን ከመባባስ በስተቀር አንዳችም ውጤት አኖረውም ማለቱ ተሰሟል፡፡
የኢራን ስም ቢነሳም እሷ ግን በዮርዳኖሱ ጥቃት እጄ የለበትም ለማለት አላረፈደም፡፡
እንደሚባለው አሜሪካ በኢራቅ እና ሶሪያ የኢራን ደጋፊ ናቸው ከምትላቸው ታጣቂዎች በተጨማሪ አብዮታዊ ዘብ የተሰኘውን የኢራን የጦር ክፍል ይዞታዎችም ዒላማዋ አድርጋዋለች፡፡
ኢራቅ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ዛሬ በሚጠናቀቅ ብሔራዊ ሐዘን ላይ ነች፡፡
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ አል ሱዳኒ ቅዳሜ እለት ብሔራዊ የሐዘን ቀናቱን ያወጁት በሰሞኑ የአሜሪካ ድብደባ ለተገደሉ ሰዎች እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
በአሜሪካ ጥቃት ታጣቂዎች የጦር ባልደረቦች እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል፡፡
በድብደባው በጥቂቱ 16 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 25ቱ ደግሞ አካላዊ ጉዳት አጋጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አል ሱዳኒ ሟቾቹን ሰማዕታት ሲሉ ጠርተዋቸዋል፡፡
አሜሪካ ድብደባዬ በኢራን ደጋፊ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ባይ ነች፡፡
ታላቋ አገር በኢራቅ እና ሶሪያ ድብደባ ለመፈፀም የተነሳችው ከሳምንት በፊት በዮርዳኖስ ወሰን በሚገኝ የጦር ሰፈሯ ላይ በተሰነዘረ የድሮን ጥቃት 3 ወታደሮቿ ለተገደሉበት አፀፋ እንደሆነ እየተናገረች ነው፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
コメント