top of page

ጥር 26 2017 - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሪፖርቱ በፌደራል ፍ/ቤቶች 84,207 መዛግብት እልባት መስጠቱን ተናግሯል

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ዕልባት እንዲሰጥባቸው የሚመጡ ጉዳዮች ቁጥር በየወቅቱ እየጨመረ በመምጣቱ ለመዛግብት በጊዜ ውሳኔ ከመስጠት አንፃር ብዙ መስራት ያስፈልጋል ተባለ፡፡


በፍርድ ቤቶች ተገልጋይ የሚፈልገዉንና የሚጠብቀዉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ከፍጥነትና ከጥራት አንፃር መልስ መመለስ በሚያስችል መንገድ መፈፀም ካልተቻለ የሚፈልገዉን ውጤት ማምጣት አስቸጋሪ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ተናግረዋል፡፡


ለዚህም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ፣ እና ክፍተት የታየባቸውን አሰራሮች በመለየት የላቀ ውጤት ላይ መድረስ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡


የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ 2017 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ሪፖርቱ በፌደራል ፍ/ቤቶች በእቅድ ከተያዙት 64,703 መዛግብት 84,207 መዛግብት እልባት መስጠቱን ተናግሯል፡፡

ይህ አፈፃፀም ካለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20,734 መዛግብት ከፍ ያለ መሆኑ ተጠቅሷል።


በአጠቃላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ዕልባት እንዲሰጥባቸው በዕቅድ ከተያዙ መዛግብት አንፃር ከፍ ያሉ አፈጻጸሞች እየታዩ ቢሆንም በየወቅቱ እየጨመረ ከመጣው የመዛግብ ፍሰት ጋር ተያይዞ እየቀረቡ ላሉ ጉዳዮች ውሳኔ ለመስጠት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡


የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የ2017 ግማሽ ዓመት እቅድ ጥሩ አፈፃፀም የታየበት መሆኑን ተናግረው ለዳኝነት ስራ አገልግሎት አሰጣጥ ቁልፍ የሆኑ ስራ ክፍሎች ላይ ልዩ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ተገልጋዩ የሚፈልገዉን አገልግሎት እንዲያገኝ መስራት ይገባል ማለታቸውን ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ሰምተናል።


ምህረት ስዩም

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page