የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የዩክሬይኑን ጦርነት ለማስቆም በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል በሚደረገው ንግግር አገሬ ልትገለል አይገባም አሉ፡፡
የዜሌንስኪ አስተያየት የተሰማው ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬይኑን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያ ሹሞች ጋር እየተነጋገርን ነው ማለታቸውን ተከትሎ እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲንን ገፅ ለገፅ እንደሚነጋግሯቸው ታውቋል፡፡
ዜሌንስኪ ዩክሬይንን ያገለለ ንግግር አሉታዊ ውጤት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ንግግሩ እኛንም ከነአቋም እና ፍላጎታችን ሊያሳትፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ወደ 3ኛ አመቱ በተቃረበው ጦርነት አሜሪካ የዩክሬይን ዋነኛዋ የጦር ደጋፊ ሆና ቆይታለች፡፡
ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻ ላይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ የዩክሬይኑን ጦርነት በአፋጣኝ አስቆመዋለሁ ሲሉ መቆየታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

በኮንጎ ኪንሻሣ M 23 የተሰኘው አማጺ ቡድን ጥቃቱን ማባባሱን የቡድን 7 አባል አገሮች አወገዙት፡፡
ቡድን ሰባቶች M 23 በኮንጎ ጦር ላይ የከፈተውን ጥቃት እንዲያቆም በጋራ መግለጫቸው እንደጠየቁ አናዶሉ ፅፏል፡፡
በዚሁ መግለጫ የሩዋንዳ መንግስት ጦርም በ M 23 አማጺ ቡድን ደጋፊነት ስሙ ተነስቷል፡፡
ሩዋንዳ በተለያዩ ወገኖች በ M 23 አማጺ ቡድን ደጋፊነት ስሟ ቢነሳም እኔ የለሁበትም ባይ ነች፡፡
የቡድን ሰባት አባል አገሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ደረጃ ባደረጉት ስብሰባ የኮንጎ ኪንሻሣ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረትም የዚሁ መግለጫ አካል ነው ተብሏል፡፡
አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ ጣሊያን እና ጃፓን የቡድን 7 አባሎች ናቸው፡፡
በሱዳን የርዕሰ ከተማዋ ካርቱም አካል በሆነችው ኦምዱርማን በአንድ የገበያ ሥፍራ ላይ በተፈፀመ የመድፍ ጥቃት በጥቂቱ የ54 ሰዎች ተገደሉ፡፡
ገበያውን ዒላማ በማድረግ በተፈፀመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ከተገደሉት ሌላ 158 ሰዎች ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ሬዲዮ ዳባንጋ በድረ ገጹ ፅፏል፡፡
ሰላማዊ ሰዎች ለተገደሉበት እና ለቆሰሉበት የገበያ ስፍራ ድብደባ የመንግስት ጦር RSF የተሰኘውን የፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት በተጠያቂነት ከስሷል፡፡
በድብደባው አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ወደ ጤና ተቋማት ተወስደዋል ተብሏል፡፡
በሌላ መረጃ ሱዳን ትሪቢዩን እንደፃፈው ደግሞ የሱዳን መንግስት ጦር በጀዚራ ግዛት ተጨማሪ 3 ከተሞችን ይዣለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ጦሩ ይዣቸዋለሁ ያላቸው ታምቡል ፣ ሩፋ እና አል ሃሳሂሣ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዩጋንዳ በሙከራ ላይ የሚገኝ የኢቦላ መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው፡፡
የሙከራ ክትባት መስጫው መመሪያው በአጣዳፊ እየተሰናዳ መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በዩጋንዳ ባለፈው ሳምንት በኢቦላ በሽታ መያዙ በምርመራ የተረጋገጠ ነርስ ሕይወቱ ማለፉ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
በዩጋንዳ የኢቦላ ወረርሽኝ ሲቀሰቀስ የአሁኑ 9ኛው ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የኢቦላ ቅኝት እና ቁጥጥሩ መጠናከሩ ተጠቅሷል፡፡
በኢቦላ ምክንያት ሕይወቱ ካለፈው ነርስ ጋር ቅርበት የነበራቸው 44 ሰዎች መለየታቸው ተሰምቷል፡፡
የሙከራ ክትባቱ በቅድሚያ የበሽታው ስጋት ለበረታባቸው 3,000 ሰዎች እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments