የግል ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች በተመለከተ የወጣው መመሪያ፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለመተግበር የሚከብዱ መስፈርቶች የተካተቱበት ነው ሲል የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ የትምህርት እና የቴክኒክና ሞያ ተቋማት ማህበር ተናገረ፡፡
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንደ አዲስ ለመመዝገብ ባወጣው መመሪያ ውስጥ አሁን ባለው ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ለመተግበር አስቸጋሪ የሆኑ መስፍርቶች የተካተቱበት ነው ብሏል ማህበሩ፡፡
በመመሪያው የሰፈሩ ሁሉንም መስፈርቶች የግድ ይተገበራሉ ከተባለም ሁሉም ተቋም በሚባል ደረጃ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ሲል ተናግሯል፡፡
ይህንን ለሸገር ራዲዮ የተናገሩት የማህበሩ የቦርድ አባል እና የሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚደንት ተረፈ ፈዬራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ዶ/ር ተረፈ እንዳሉት ከሆነ ከተቀመጡ #መስፈርቶች ስንት በመቶ ያሟላው ነው የሚቀጥለው የሚለው ራሱ በግልጽ አልተቀመጠም ብለዋል፡፡
‘’ሁሉንም ያላሟላ አይመዘገብም የሚባል ከሆነ አስቸጋሪ ነው ምክንያቱም መስፈርቶቹ ብዙ ስለሆኑ አንዱ ቢያሟሉ እንኳ በሌላኛው ሊያጓግል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው’’ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
መመሪያው እንደወረደ ይተግበር ከተባለም የግሎቹ ብቻ ሳይሆኑ የመንግስቶቹም የማያሟሉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡
መመሪያውን አይተው ከዘርፉ ከወጡ ተቋማት በተጨማሪ፤ አሁንም እስኪ #እንሞክር ብለው የገቡ ተቋማት ብዙ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡
መመሪያውን በማየት እኔ ይህንን አላሟላም ብለው በጊዜ የወጡ ተቋማት አደንቃለሁ ያሉት የቦርድ አባሉ የሚዘጉ ተቋማት ከዘርፉ ሲወጡ አወጣጣቸው እንዴት ይሁን የሚለው በጣም ጥንቃቄ የሚሻ ነው ብለዋል፡፡
አዲሱ መመሪያን ጨምሮ በትምህርት ዘርፍ ጥራት ለማስጠበቅ የተለያዩ ማሻሻያዎች መደረጋቸው የሚያበረታቱት ዶ/ር ተረፈ ነገር ግን ለመተግበር አስቸጋሪ የሆኑ መመሪያዎች መኖራቸው በተለይ ለግሉ ዘርፍ እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ያስረዳሉ፡፡
በአዲሱ መመሪያ ለመተግበር አስቸጋሪ ናቸው ብለው ከጠቀሷቸው መካከል #የመጫወቻ_ሜዳ አንዱ ነው፡፡ ተቋማቱ አብዛኞቹ ሚከራዩት ህንጻ ነው የሚከራዩት ህንፃ አካባቢ ደግሞ የስፖርት ማዘውተሪያ አይሆራቸውም ይህ እንዴት ሊታይ ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
የመምህራን እና የሰው ሀብት በተመለከተ የተቀመጠው መስፍርትም ለመተግበር አስቸጋሪ ከሆኑት መካከል ሌላኛው እንደሆ አነስተዋል፡፡
ስታንዳርዱ ሲዘጋጅ እንድታዩትና ሀሳብ እንድታዋጡ አልተደረገው ወይ ያልናቸው ዶ/ር ተረፈ መመሪያው ሲዘጋጅ አይተነዋል፣ መሻሻልና መስተካከል አለበት ያልነውን የመፍትሄ ሀሳቦች አቅርበናል፤ ተግባራዊ የተደረጉት ግን በጣም ውስኖቹ ናቸው ብለዋል፡፡
ለመተግበር አስቸጋሪ ናቸው ስለተባሉ መስፈርቶች በተመከተ #የትምህርትና_ስልጠና_ባለስልጣንን ጠይቀናል፡፡
በባለስልጣኑ የፈቃድ አሰጣጥ እና የጥራት ኦዲት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ውብሸት ታደለ፤ የወጡ መስፈርቶች የዘርፉን አጠቃላይ ሁኔታ በማየት፤ ማሟላት አለባቸው ከሚባሉት ዝቅተኛ የተባሉት መስፈርቶች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡

የመውጫ ፈተና ከሚፈተኑት መካከል እያለፉ ያሉት በጣም ጥቂቶቹ እንደሆ እየታየ ነው፣ ያ ማለት ባለፉት ዓመታት በአግባቡ ያልተማረ የሰው ሀይል ነው ገበያውን ሲቀላቀል የነበረው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በተለይ በግሉ ዘርፍ የነበረው ስርዓት የሚታወቅ ነው፣ ማንም የተወሰነ ክፍሎች ያሉት #ህንፃ እየተከራየ ኮሌጅ ይክፍት ነበረ አሁን የሚተገበረው ስርዓት ግን ይህንን አይፈቅድም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ብዙዎቹ የተቀመጠው መስፍርት የሚጎድላቸው ከሆነ እንደ መፍትሄ የታሰበ አማራጭ ይኖር እንደሆነ የጠየቅናቸው ሀላፊው፤ የተቀመጠው መመሪያ ላይ እንደ የሁኔታው አይተን እና ነባራዊ ሁኔታዎችን እያገናዘብን እንዳንድ የምንፈቅዳቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ብለውናል፡፡
አቅም ኖሯቸው የተወሰኑ መስፈርቶች የማያሟሉትን ትንሽ መስፈርቶችን አላሟላችሁም ብለን ከገበያው እንዲወጡ አናደርጋቸውም፣ እንዳያሟሉ ድጋፍ እናደርግላቸዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ብዙ አቅም የሌላቸው እና ለትምህርት ያላቸው አመለካከት እምብዛም የሆኑ ሰዎች የስራ መስክ እንዲቀይሩ መክረዋል፡፡
የሚደረገው ጥረት ለትምህርት ጥራት ሲባል በመሆኑ ሁሉም ይህንን ሊረዳ ይገባልም ብለዋል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments