ከዋሽንግተኑ የአውሮፕላን እና የሔሊኮፕተር ግጭት አደጋ እስካሁን አንድም በሕይወት ተራፊ አልተገኘም ተባለ፡፡
የተጋጩት የመንገደኞች አውሮፕላን እና የጦር ሔሊኮፕተር በፖቶማክ ወንዝ ውስጥ መውደቃቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
አውሮፕላኑ ሰራተኞቹን ጨምሮ 64 ሰዎችን ሔሊኮፕተሩ ደግሞ 3 የጦር ባልደረቦችን አሳፍረው ነበር፡፡
የአደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም፡፡
የአውሮፕላኑ እና የሔሌኮፕተሩ የበረራ ሒደት መመዝገቢያ ሳጥኖች /ብላክ ቦክሶች/ ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
መጥፎ የአየር ሁኔታ የነፍስ አድን ጥረቱ እንዲገታ ማስገደዱ ተሰምቷል፡፡
ገና የአደጋው የምርመራ ውጤት ሳይታወቅ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አደጋው የቀዳሚው አስተዳደር የተዋፅኦ ማመጣጠኛ የቅጥር መላ ውጤት ነው ማለታቸው እያወዛገበ ነው፡፡
የበረራ ደህንነት አካሉ የበላዮች ግን ስለ አደጋው መንስኤ ለመናገር ጊዜው ገና ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የምርመራውን የቅድሚያ ውጤት ለማወቅ በጥቂቱ የ30 ቀናት ጊዜ ያሻል ማለታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ በጎንጎው ጦርነት የተነሳ ግንኙነታቸውን በጣሙን እየደፈረሰ ነው ተባለ፡፡
የM 23 አማጺ ቡድን ሰሞኑን በምስራቃዊ ኮንጎ ኪንሻሣ ትልቋ የሆነችውን የጎማ ከተማን መቆጣጠሩ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
በዚህ ውጊያ በምስራቃዊ ኮንጎ ኪንሻሣ ሰላም ለማስከበር ከተሰለፉት መካከል 13 ደቡብ አፍሪካውያን መገደላቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ይሄን ተከትሎም የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሣ ሩዋንዳ አማጺያኑን መርዳት ማቆም እንዳለባት ተናግረዋል፡፡
ሩዋንዳ M 23ን በመርዳት እና በመደገፍ ስሟ በተደጋጋሚ እየተነሳ ነው፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች ተልዕኳቸው ሰላም ማስከበር ሳይሆን ከኮንጎ መንግሰት ጦር ጎን ተሰልፎ መዋጋት ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ደቡብ አፍሪካ የአስታራቂነትም ሆነ የሽምግልና ሚና ሊኖራት አይገባም ማለታቸው ተሰምቷል ካጋሜ፡፡
የጎንጎው ጦርነት አድማሱ እየሰፋ መምጣቱ ይነገራል፡፡
አለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (INTERPOL) በምዕራብ አፍሪካ በብርቱ ብርቱ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 45 ሰዎችን ይዤ አስሬያለሁ አለ፡፡
ግለሰቦቹ የተያዙት በአደገኛ እፅ ማስተላለፍ እና በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት እንደሆነ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙባቸው አገሮች መካከል ማሊ ፣ ኒጀር ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኬፕቬርዴ ከብዙ በጥቂቱ መሆናቸው ታውቃል፡፡
ግለሰቦቹ ፈፅመውታል የተባለው ወንጀል ጥልፍልፎሹ የበዛ እና አለም አቀፋዊ ገፅታ ያለው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ኢርተርፖል 45 ተጠርጣሪዎችን የያዘው ባለፉት 3 ወራት ነው ተብሏል፡፡
የወንጀል መረቡ ጥልፍልፍ ለአገሮች ብሔራዊ ደህንነትም አስጊ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኮንጎ ኪንሻሣ የአማጺያን ጥምረት ዘመቻችን ጎማን በመያዝ ብቻ አይገደብም ገና መላ አገሪቱን እንቆጣጠራለን ሲል ዛተ፡፡
እንደሚባለው የM-23 አማጺ ቡድንም የዚሁ ጥምረት አካል እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡
የአማፂያኑ ጥምረት መሪ ኮርኒል ናንጋ ገና ርዕሰ ከተማዋ ኪንሻንም መያዛችን አይቀርም ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኮንጎው ጦርነት አድማስ መስፋት በእጅጉ አሳስቦኛል እያለ ነው፡፡
በዚህ ጦርነት ሩዋንዳ ስሟ በአማፂያኑ ደጋፊነት በእጅጉ በክፉ እየተነሳ ነው፡፡
አንጎላ ፣ ቻይና ፣ ፈረንሳይ ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በየፊናቸው ሩዋንዳ ወታደሮቿን ከኮንጎ ኪንሻሣ እንድታስወጣ ጠይቀዋል፡፡
የሩዋዳው ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ ግን የM-23 ታጣቂዎች የኮንጎ ኪንሻሣ እንጂ የሩዋንዳ ዜጎች አይደሉም የሚል መሟገቻ እያቀረቡ ነው፡፡
የኔነህ ከበደ
ቴሌግራም: https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Comentários