top of page

ጥር 22፣2016 - የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በብርቱ እየተሰራ ነው ተባለ

የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ለማስመዝገብ በብርቱ እየተሰራ ነው ተባለ፡፡


በየዓመቱ ጥር 23 በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል ከሀገር እውቅና አልፎ ለአለም ለማስተዋወቅ በተለይም በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ሁሉ ተሟልተው ለፌደራል መንግስት መላኩን የአገው ፈረሰኞች ማህበር አስረድቷል።


በዚህ ዓመት መጨረሻ በዩኔስኮ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም የማህበሩ ሊቀ መንበር አለቃ ጥላዬ አየነው ነግረውናል፡፡


ከ62,000 በላይ አባላቶች አሉት የተባለው ማህበሩ አባለቱን 150,000 ለማድረስ እየተጋ ነው ተብሏል፡፡


በዘንድሮው የፈረሰኞች ውድድር የሚሳተፉ ፈረሰኞች ቁጥር ከአምናው በግማሽ ያህል እንደሚቀንስም ሰምተናል፡፡

አምና እስከ 6000 ፈረሰኞች በውድድሩ ተሳትፈው ነበር የተባለ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን ቢበዛ ከ3000 እንደማይበልጡ አለቃ ጥላዬ ተናግረዋል፡፡


ይህ የተወዳዳሪዎች ቁጥር መቀነስ በክልሉ ካለው አለመረጋጋት ጋር የሚያያዝ ሳይሆን በእራሴ መስፈርት የተወዳዳሪዎች ቁጥር በመቀነሴ ነው ሲል ማህበሩ ለሸገር ነግሯል።


በውድድሩ ሴት ተሳታፊዎችም እንዳሉ አለቃ ጥላዬ አውርተውናል፡፡


የአገው ፈረሰኞች ማህበር በ1930 የተመሰረተ ሲሆን በነገው ዕለት የ84ኛ ዓመት በዓሉን በእንጅባራ ከተማ ያከብራል ተብሏል፡፡ማንያዘዋል ጌታሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…Comments


bottom of page