አክሽን አጌንስት ሀንገር (Action Against Hunger) የተሰኘው አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት፤ በኢትዮጵያ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህፃናት እና እናቶች ያቀርብ የነበረውን እርዳታ እንዲቆም ትዕዛዝ እንደተሰጠው ተሰማ፡፡
ተቋሙ በኢትዮጵያ ያለውን ጣቢያ ለመዝጋት እየተዘጋጀ ነውም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ለተጠለሉ ስደተኞች ያቀርብ የነበረው የምግብ እርዳታ እንዲቋረጥ ባለፈው አርብ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በስደተኞችና ፍልስተኞች ጉዳይ ቢሮ በኩል ለእርዳታ ሰጭው ተቋም ደብዳቤ እንደደረሰው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ተቋሙ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት እና ለእናቶቻቸው የአልሚ ምግብ እርዳታ ያቀርብ ነበር ተብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለውጭ ሀገራት የምትሰጠው እርዳታ ከውጭ ፖሊሲዋ እና ቅድሚያ ከምትሰጣቸው አጀንዳዎቿ ጋር የተጣጣመ መሆኑን እንደገና ለመገምገም የውጭ እርዳታን ለ90 ቀናት ማገዳቸው ይታወቃል፡፡
የተጠቀሰው የረድኤት ድርጅትም በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰራ እንደመሆኑ እገዳው የሚመለከተው ሆኗል ተብሏል፡፡
ይህን ተከትሎ ነው ድርጅቱ ለስደተኛ ህፃናት እና እናቶችን ያቀርብ የነበረውን እርዳታውን እንዲያቆም የተደረገው ተብሏል፡፡
ይህ ተቋም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ የከፋ የምግብ እጥረት የነበረባቸውን ሶስት ሺህ ህፃናት ሲመግብ ቆይቷል ተብሏል፡፡

በአጠቃላይ ከደቡብ ሱዳን ጋር በምትዋሰነው በጋምቤላ ክልል የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የተጠለሉ ለ400 ስደተኞች የምግብ እርዳታ እንደሚያቀርብም ተሰምቷል፡፡
ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መ/ቤት የደረሳቸውን ውሳኔ ተከትሎም የረድኤት ድርጅቱ በጋምቤላ ያለውን የምገባ ማዕከል ለመዝጋት ዝግጅት ላይ መሆኑን ሮይተርስ ጠቅሷል፡፡
በነገራችን ላይ ባለፈው ዓመት በጋምቤላ ክልል የተጠለሉ ስደተኞች ባጋጠማቸው የምግብ እጥረት ምክንያት ወደ ከተማ ወጥተው ከነዋሪው ማህበረሰብ ጋር እስከመጋጨት ደርሰው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያና ከሌሎችም ሃገራት የመጡ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን ማስጠለሏ ይታወቃል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Comments