ጥር 20 2017 - በተለያዩ አካባቢዎች 75 አባላቶቹ እንደታሰሩ ኢዜማ ተናገረ
- sheger1021fm
- Jan 28
- 1 min read
በተለያዩ አካባቢዎች 75 አባላቶቹ እንደታሰሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተናገረ፡፡
እየተፈፀመ ያለው ውክቢያና እስር ሰላማዊ ትግሉን አደጋ ላይ የሚጥልና ወደ ሌላ አማራጭ የሚገፋ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
ኢዜማ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የታሰሩ አባላቶቹ በአፋጣኝ እንዲፈቱለም ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ5 ወር በላይ የቆዩ መኖራቸውንም ፓርቲው ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የታሰሩ አባላቶቹ ላይ የሚፈፀመው ውክቢያ ሊቆም ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡
ፓርቲው እየተፈፀሙ ያሉ እስራቶች እና ውክቢያዎች ወደ ቀድሞ አዙሪት የሚከቱ ስለሆነ ሰላማዊ ትግል በሚያራምዱ አባላቶቹ ላይ የሚፈፀመው እስር ሊቆም ይገባል ብሏል፡፡
የኢዜማ የህግ እና አባላት ደህንነት መምሪያ ሀላፊ የሆኑት አቶ ስዩም መንገሻ አሁን በፓርቲው አባላቶች ላይ እየተፈፀሙ ያሉ እስራት እና ውክቢያዎች ሰላማዊ ትግሉን አደጋ ላይ የሚጥሉና ሌላ አማራጭ እንድናይ የሚገፋ ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡

ኢዜማ ስሜታዊነት የሚያጠቃው ፓርቲ እንዳልሆነ ይታወቃል ያሉት አቶ ስዩም በዚህም እቅድ ነው እየሰራን ያለው ብለዋል፡፡
“እዚህ አገር ላይ በምክንያት፣ በሀሳብ የበላይነት የፖለቲካ ውድድር ተደርጎ መንግስት በዚያ መንገድ ነው መለወጥ ያለበት ብሎ አምኖ እየታገለ ያለ ፓርቲ ነው'' ያሉት የኢዜማ የህግ እና አባላት ደህንነት መምሪያ ሀላፊ የሆኑት አቶ ስዩም መንገሻ ይሁንና አሁን እየተፈፀሙ ያሉ ድርጊቶች ግን ሌላ አማራጭ እንድናይ የሚያስገድድ ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና የፖለቲካ አባላቶችን በየቦታው ባንገላታን ቁጥር የሚመጣው የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ነው የዲሞክራሲ ሒደትን ማቆም ነው ስለዚህ ከዚህ ችግር ለመውጣት ደግሞ የሰላማዊ ትግል አራማጆች ላይ የሚፈፀሙ ውክቢያዎች እና እስራቶች ሊቆሙ ይገባል የታሰሩትም መፈታት አለባቸው ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካው ሜዳ ላይ እንዲጫወቱ የሚያደርጉ ሒደቶች ይደነቃቀፋሉ ይህ ደግሞ መልሶ ወደ ቀድሞ አዙሪት ይከተናል ብለዋል፡፡
እዚህ አገር ላይ የነበረው በጦርነት ወይም በአብዮት ነው ይህ ነገር ይቁም ከተባለ ደግሞ በሀሳብ የበላይነት መሆን አለበት የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት አለበት የመደራጀት መብትም መፈቀድ አለበት ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comentários