በአማራ ክልል ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የክልሉ መንግስት ያቀረበው የሰላም ጥሪ እንጂ እጅ ስጡ አላለም፤ የክልሉ መንግሥት እጅ ስጡ አለ እየተባለ የሚናፈሰውም የውሸት አሉባልታ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ፡፡
የክልሉ መንግሥት ለሰላም እጁን ከዘረጋ ከየትኛውም ኃይል ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነውም ብለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ ከባህርዳር የኮማንድ ፖስት ኃላፊዎች እንዲሁም በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ተጠርጥረው በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት በህግ ጥላ ስር ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጋር ውይይት መድረጉ ተሰምቷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በውይይቱም ወቅት፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የተሻለ ለማድረግ በተደጋጋሚ ከሕዝብ ጋር የውይይት መድረክ እየተደረገ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ለታጠቁ ኃይሎች የሰላምና የምህረት ጥሪ በማቅረብ እንዲሁም ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
የተደረገው የሰላም ጥሪ በሕገ መንግሥቱ ይቅርታ ከማይደረግላቸው ወንጀሎች ውጭ ከዚህ ቀደም የነበሩ ወንጀሎችን ይቅርታ እንደሚያሰጥም አንስተዋል።
የባህርዳር ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ሙሉአለም አድማሱ በበኩላቸው ኮማንድ ፖስቱ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከተያዙ ተጠርጣሪዎች መካከል የተሃድሶ ስልጠና በመስጠትና በመምከር ወደ ሕብረተሰቡ የተቀላቀሉ መኖራቸውን አስረድተው፤ ለፍርድ የሚቀርቡ ተጠርጣሪዎች ልየታና የምርመራ ሂደት ተጠናቆ ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝም መናገራቸውን ከህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት ሰምተናል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments