በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ ለመጣው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ መለወጫ ምን ታስቧል? የሚል ጥያቄ የኢንዱስትሪ ሚንስቴር ተጠየቀ፡፡
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህን የተጠየቀው የስድስት ወር ስራ ክንውኑን ለህዝብን እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ፈቲ ማሃዲ በሃገሪቱ #የኤልክትሪክ_መኪና_መገጣጠሚያ_ፋብሪካዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በክልሎችም ጭምር እየጨመረ መምጣቱን መልካም ነው ምክንያቱም ሃገሪቱ በየአመቱ ለነዳጅ የምታወጣውን 4 ቢልዮን ዶላር ያስቀራል ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች እየበረከቱ ቢመጡም የባትሪው ጉዳይ ግን ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪኖች የተወሰነ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ባትሪያቸው እየደከመ ይመጣል ያሉት አቶ ፈቲ መሃዲ አሁን ባለው አለማቀፍ ገበያ ደግሞ የአንድ ኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ከ5,000 እስከ 10,000 #ዶላር ነው ይህም ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር ይጠጋል ስለዚህ በሃገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ማምረቻ ማቋቋም ወሳኝ ሆኖ ይታያል ብለዋል፡፡
ወደ ፊት ለባትሪ የሚወጣው ውጪ ምንዛሪ ፈታኝ እንዳይሆን በሃገር ውስጥ ለማምረት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምን እየሰራ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ለባትሪ ማምረት የሚረዳ ሊትየም እና ሌሎች ማዕድኖች አሏት ይህንን ተጠቅመን በሃገር ውስጥ ባትሪ ለማምረት ከሚመለከታቸው እና በዚህ ዘርፍ ላይ ለማምረት አቅም ካላቸው ጋር ውይይት እያደረግን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Commentaires