ግንቦት 8 2017 - የጤና ሚኒስቴር በስራ ገበታቸው ያልተገኙ የጤና ባለሞያዎች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ አሳሰበ፡፡
- sheger1021fm
- May 16
- 2 min read
የጤና ሚኒስቴር በስራ ገበታቸው ያልተገኙ የጤና ባለሞያዎች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ አሳሰበ፡፡
ወደ ስራ ገብታቸውም በማይመለሱት ላይ ርምጃ እወስዳለሁ አለ፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው፣ የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ አለን ብለው የስራ ማቆም አድማ የጀመሩ የጤና ባለሞያዎችን አስመልክቶ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው።
ጤና ሚኒስቴር ለመግለጫው መነሻ የሆነው ፣ የሕክምና ባለሙያዎች ሊያኖረን አልቻለም፤ ያሉት የደመወዝ ማነስና ጥቅማ ጥቅም እንዲሻሻል ያቀረቡት ጥያቄ፣ ስላልተመለሰ የሥራ ማቆም አድማ መጀመራቸው ነው፡፡
የጤና ባለሞያዎች ፣የስራ ማቆም ማድረጋቸውን መምታት “ብዙዎቹ በሐሰተኛ መረጃ ተወናብደው፣ ጥቂቶቹ ደግሞ ጥፋትን ዓላማቸው በማድረጋቸው ነው” ሲል ጤና ሚኒስቴር ተችቷል፡፡
ከህግ አኳያም የጤና ሞያ የስራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የስራ ዘርፎች መካከል እንደሆነ የጠቀሰው ጤና ሚኒስትር፤ የጤና ባለሞያዎቹ ጥያቄ እንኳን ቢኖራቸው በስራ ገበታቸው ላይ ተገኝተው መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቅሷል፡፡
ባለሞያዎቹ ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰው ማህበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ በየተቋማቱ ጥሪ መደረጉንም አስታውሷል።
መንግስት የጤና ባለሞያዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ የተለያዩ ህጎችን እንዳወጣ ያስታወሰው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ፣ በጎ ህሊና ያላቸው የጤና ባለሞያዎች ይህንኑ በመገንዘብ ስራቸውን እንዲያከናውኑ፣ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል።
የምንሰራው ስራና የሚከፈለን ደመወዝ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ መኖር እያቃተን ነው ያሉ የጤና ባለሞያዎች ወደ ከፊል የስራ ማቆም አድማ የገቡት ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ መሆኑ ይታወሳል።
የጤና ባለሞያዎቹ ወደ ስራ ማቆም አድማው የገቡት፣ ምላሽ እንፈልግባቸዋለን ያሏቸውን አስራ ሁለት ጥያቄዎች ዘርዝረው ለጤና ሚኒስቴር ካስገቡ ከአንድ ወር በኋላ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡
እስከ መጪው ሰኞ ይዘልቃል ባሉት ከፊል የስራ ማቆም አድማም ማህበረሰቡ እንዳይጎዳ፣ የድንገተኛ ህክምና ፣የማዋለድ አገልግሎትና የቀዶ ጥገና ህክምና እየሰጡ እንደሚቆዩ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

መንግስት በሆደ ሰፊነት ችግሩን ለመፍታት ያሳየውን ትዕግስት ወደ ጎን በማለት በስራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ እንዲሁም በጤና ተቋምም ሆነ ከጤና ተቋም ውጪ ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩት ላይ አስፈላጊ የሆነ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ቀድመን እናሳውቃለን ሲል ጤና ሚኒስቴር በመግለጫው አሳስቧል።
ጥያቄያችን የፖለቲካ ሳይሆን የመኖር ጥያቄ ነው የሚሉት የሕክምና ባለሙያዎቹ በበኩላቸው ምላሽ አላገኘንም ብለው የስራ ማቆም አድማውን ለማድረግ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡
የሕክምና ባለሙያዎቹ የሚፈለን ደመወዝ፣ ሊያኖረን አልቻለም የሚለው ብሶታቸው ይስተካከልን የሚሏቸው ጥያቄዎች በተለያዩ በተለያየ የሃገሪቱ ክፍሎች ባሉ ሙያተኞች ሲንፀባረቅ ታይቷል፡፡
ይህንኑ የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ባለሞያዎቹ በአስቸኳይ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያሳስቡ ማስታወቂያዎች በጥቁር አንበሳ ፣ በጳውሎስ ፣ በጎንደርና በሌሎችም የጤና ተቋማት ተለጥፈው ታይተዋል።
ግን ማስታወቂያዎቹ እንዳሳሰቡት ባለሙያዎቹ ስራ አልጀመሩም፡፡
በማግስቱ ረቡዕ ዕለትም የጤና ሚኒስትር ድኤታው ዶክተር ደረጀ ድጉማ በቅዱስ ጳውሎስ እና በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ተገኝተው በስፍራው የነበሩ የጤና ባለሞያዎችን ማነጋገራቸውን ሠምተናል።
የንግግራቸው ውጤት ግን ይፋ አልሆነም፡፡
በትላንትና የሚኒስቴሩ መግለጫ ባለሙያዎቹ ወደስራቸው እንዲመለሱ አሳስቧል፡፡
በማይመለሱት ላይ ርምጃ እንደሚወስድ ተናግሩዋል፡፡
ግን ርምጃው ምን እንደሆነና ከመቼስ እንደሚጀምር በመግለጫው አልተጠቀሰም፡፡
በትናንቱን የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው እና ስሜ አይገለጽ ያሉ አንድ የጤና ባለሞያ አድማውን የተሳተፉት የተወሰኑ ሰዎች ናቸው የሚለው ጤና ሚኒስቴር መግለጫ ጥያቄውን ለማሳነስ የተደረገ በመሆኑ አሳዝኖናል ይላሉ፡፡
የጤና ባለሙያዎቹ በአድማው ታሳታፊ የሆኑ የጤና ባለሞያዎች በፀጥታ አካላት እየታሰሩ መሆናቸውን፣ በአንዳንድ የጤና ተቋማት ለስፔሻሊቲ እና ለሰብ ስፔሻሊቲ እየተማሩ ለሚሰሩ ዶክተሮች የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት እንዲለቁ እየተደረገ መሆኑን ፣የሞያ ሰርፈቲኬታችሁን ትነጠቃላችሁ፣ መባላቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
መንግስት በሠላማዊ መንገድ ከአመታት በፊት ጀምሮ እያነሳን ላለነው ጥያቄ ተነጋግሮ በሠላም ለመፍታት ቢሰራ መልካም ነው ያሉት የጤና ባለሞያው ባለሙያዎቹም ለዚህ ዝግጁ መሆናችንን ቀድመው ማሳወቃቸውን ይናገራሉ፡፡
ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ የጤና ባለሙያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለመስጠት ቀደም ብሎ ማፅደቁንና ደንበኛ መመሪያዎች በማውጣት ትኩረት ሰጥቶ መሰራቱን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
ህብረተሰቡም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎች ሳይሸበር የሚፈልገውን የጤና አገልግሎት በተለመደው መልኩ በጤና ተቋማት ማግኘት እንደሚችል አመልክቷል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
コメント