ግንቦት 7 2017 - ኢትዮ ቴሌኮምና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚንስቴር ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ ሶስት የዲጂታል ሶሉሽኖችንም ወደ ስራ አስገብተዋል
- sheger1021fm
- May 15
- 2 min read
ኢትዮዽያ በዓለም ፊት በክፉ ስሟን የሚያስጠራትን የትራፊክ አደጋ ብዛት በእጅጉ የሚቀንስ የዲጅታል መፍትሄ ወደ ስራ አስገባች።
የኢትዮዽያ አሽከርካሪዎች ከእንግዲህ በምታሽከረክሩበት፣ በሀገሪቱ አውራ ጎዳና ጥፋት አጥፍታችሁ ብትገኙ፣ ቅጣታችሁን በዲጅታል መንገድ መክፈል የምትችሉበት መላ ተበጅቷልም ተብሏል።
በማሽከርከር አጋጣሚ ፤ ጥፋት ተገኝቶ ለጥፋቱ አይነት የተተመነውን ቅጣት ለመክፈል የነበረውን እንግልት ያስቀራል የተባለ ዘመናዊ መንገድ መሰናዳቱን የሰማነው፤ ኢትዮ ቴሌኮም እና እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አገልግሎቱን በጋራ ወደ ስራ ባስገቡበት ዝግጅት ላይ ተገኝተን ነው።
ይህ የዲጅታል ስርአት በብሔራዊ ደረጃ ከትራፊክ ቅጣት ባለፈ፤ የአሽከርካሪዎችን ሙሉ መረጃ በመመዝገብ ለመያዝ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
ይህም በትራፊክ ህግ ጥሰት የሚወድመውን ሀብትና የሚጠፋውን የሰው ህይወት ይታደጋል፣ የአሽከርካሪዎችን መረጃም በሀገር ደረጃ ለመያዝ ያስችላል ተብሏል።
አገልግሎቱ ወረቅት እየበጠሱ መንጃ ፈቃድ እየነጠቁ መቅጣትን የሚያስቀር፣የነበረውን የተዝረከረከ አሰራርም ወግ የሚያስይዝ ነው መባሉን ሰምተናል።
ይህም በመሆኑ የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በሐገሪቱ የሚመድባቸውን ሙያተኞች ፤ወደ ዘመናዊ አሰራር የሚያስገባቸው ሲሆን፤ ማሽከርከር ስራቸው እና እንጀራቸው የሆኑ ኢትዮዽያውያን በቅጣት መክፈልና መንጃ ፈቃድ መቀበል ምክንያት ያገኛቸው የነበረው መንከራተት ያስቀርላቸዋል ተብሏል።
ይህ አገልግሎት ሌብነትን ያርቃል ፤ ሀሰተኛ የማሽከርከርያ ፈቃድ ለመቆጣጠር ይረዳል፣የሚባክን ሀብትና ግዜን ያስቀራል፤ ጭቅጭቅ ወከባ እና ንትርክንም ይቀንሳል መባሉን ሰምተናል።
ኢትዮ ቴሌኮም እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚንስቴር ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ ሶስት የዲጂታል ሶሉሽኖችንም ወደ ስራ አስገብተዋል።

እነዚህም የሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ስርአት፤ የተቀናጀ ነዳጅ አቅርቦት ስርዓት እና ሐገር አቀፍ የትራፊክ ቅጣት ማዕከላዊ አስተዳደር ስርአት መሆናቸውን ሰምተናል።
ይህን አገልግሎት በድረ ገፅ ፤ በሞባይል መተግበሪያ እና በአጭር የፅሁፍ መልእክት አማካኝነት ማግኘት ይቻላል ተብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ስርአት በመላው ሐገሪቱ ለመጠቀም የሚያስችል በቂ የዳታ ሥርአት አስተዳደር እና ተያያዥ የጀርባ ስራዎችን ለማከናወን የምችልበትን ጉልበት እና መሳሪያ ታጥቄያለሁ ሲል አረጋግጧል።
በዛሬው ፕሮግራም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ይህ የዲጅታል መላ፣የሚጠፋውን ግዜና ሐብት ከማዳን ባለፈ በኢኮኖሚው የደም ሥር የሆነውን የትራንስፖርት ስርአት ወግ ያስይዛል ብለዋል።
በዚህ ጉባኤ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ በበኩላቸው የዲጅታል አገልግሎቱ ፤በዚህ ዘርፍ ኢትዮዽያ አለም የደረሰበትን ዘመናዊ መላ ተግባራዊ እንድታደርግ ያግዛታል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ በቴሌ ብር ባስጀመረው የትራፊክ ቅጣት በአንድ ዓመት ብቻ ከ 3.3 ሚሊየን አሽከርካሪዎች ከ 6 ሚሊየን በላይ ቅጣት መመዝገቡ ተሰምቷል።
በዚሁ አንድ ዓመት በቴሌ-ብር በተደረገ የትራፊክ ቅጣት 1.86 ቢሊየን ብር ተሰብስᎆል ተብሏል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
Comments