top of page

ግንቦት 5፣2017 - በረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ ማቆም ምክንያት የጤናው ዘርፍ የገጠመው የበጀት ጉድለት እንዴት ይሞላ የሚለው እየተመከረበት ነው፡፡

  • sheger1021fm
  • May 13
  • 2 min read

በጤናው ሴክተር የተከሰተውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ምን ይደረግ በሚለው ጉዳይ ላይ የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማህበር ይመለከታቸዋል ያላቸውን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ጠርቶ አወያይቷል፡፡


ትልቁ የስነ ተዋልዶ ጤና ግብዓት አቅራቢ የነበረው ዩኤስ ኤ አይዲ የሚሰጠውን ድጋፍ በድንገት ማቆሙ እንዲሁም ሌሎችም ሃገራት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ድጋፋቸውን እየቀነሱ መሆኑ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ እንዳይሆን በጀት የማፈላለጉ ስራ ይበርታ ተብሏል፡፡


በልገሳ ከሚገኘው የጤናው ዘርፍ ሃብት ግማሽ ያህሉን ለቤተሰብ እቅድ፣ ለእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት በሚውልባቸው ባለፉት ዓመታት እንኳን የኢትዮጵያ የስነ ተዋልዶ ጤና ሽፋን 41 በመቶ ነው፤ለቀሪ 59 በመቶ እናቶች እና ህፃናት አገልግሎቱን ማዳረስ አልተቻለም ተብሏል፡፡


በመሆኑም ይህ በልገሳ ሲገኝ የነበረው ሃብት በሌላ ካልተተካ የስነ ተዋልዶ ጤና ሽፋኑ ከዚህም ሊያሽቆለቁል የሚችል መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡


በሚኒስቴሩ የስነ ተዋልዶ ጤና፣የቤተሰብ እቅድና የአፍላወጣቶች ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ታደለ ከበደ እንደሚሉት አገልግሎቱን ከ60 በመቶ በላይ ለሆኑ ሰዎች ማድረስ ስላልተቻለ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ የህፃናት እርግዝና 13 በመቶ ላይ ነው፤


በሌላ በኩል በሃገሪቱ ከሚወልዱ እናቶች መካከል የቤተሰብ እቅድ ባለመጠቀማቸው ምክንያት በአማካኝ አንድ ልጅ ሳይፈልጉ እንደሚወልዱ የስነ ህዝብ ጤና ጥናት ያሳያል ይላሉ፡፡


አብዛኛው ለእናቶችና ህፃናት የሚሰጠው መድሃኒትም ይሁን ክትባት በእርዳታ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው የህፃናትና እናቶች ሞት ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን የነገሩን በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የምክር ቤት አባሉ ዶ/ር አብርሃም አለማየሁ፤


እርሳቸው ምክትል ሰብሳቢነት የሚመሩት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትኩረት እንደሰጠው ነግረውናል፡፡


የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የጤና ሚኒስቴር ያጣው በጀት ምን ያህል እንደሆነ በዝርዝር በማቅረብ ከመንግስት ወጪ ለመሸፈን እንዲያስችል ህጎችና ደምቦችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል የሚሉት ምክትል ሰብሳቢው ይህ ሁሉ ተዘጋጅቶ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ከቀረበ ተወያተን መፍትሄ ለማፈላለግ ዝግጁ ነን ሲሉም አስረድተዋል፡፡


መንግስት ጉድለቱን ለመሸፈን ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የግል ባለሃብቶችን አቅም መጠቀም፣መድሃኒቶችን በሃገር ውስጥ ማምረት ላይ መበርታት እንደሚያስፈልም ጠቅሰዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የስነ ተዋልዶ ጤና፣የቤተሰብ እቅድና የአፍላ ወጣቶች ጤና ባለሙያው ዶ/ር ታደለ ከበደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ከብሪክስ አባል ሃገራት ጋር ስምምነት ላይ እየተደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


በኢትዮጵያ የተዋልዶ ጤና አገልግሎት አልደረሳቸውም የተባሉት 61 በመቶ ሰዎች እያሉ በተጨማሪም በየዓመቱ 794 ሺህ አፍላ ወጣቶች የተዋልዶ ጤና አገልግሎት የሚፈልጉበት እድሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡


ስለሆኑም በየአመቱ ለሚጨምረው ፍላጎት ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት ለመስጠትና እንቅፋት የሆነውን የበጀት እጥረት ለመቅረፍ ስራዎች በህግ ማዕቀፍ ሊደገፉ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳስበዋል፡፡


ምንታምር ፀጋው

コメント


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page