top of page

ግንቦት  5፣2016 - ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ ሀብት ቢኖራትም አውጥታ መጠቀም አለመቻሏ ብዙ እያሳጣት ነው ተባለ

ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ ሀብት ቢኖራትም አውጥታ መጠቀም አለመቻሏ ብዙ እያሳጣት ነው ተባለ፡፡

 

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዘጋጅቶ እያተደረገ ባለው ኢትዮጵያ ታምርት ኤግዚቢሽን ላይ ዘርፉን ለማሳደግ ምክክሮች ጎን ለጎን እየተደረገ ሲሆን በተለይም ከኃይል አቅርቦትና ተደራሽነት እንዲሁም ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ ያላት ሀብት አውጥቶ ለገብያ ከማቅረብ አኳያ ያለባት ክፍተት ተነስቷል፡፡

 

የማዕድን ሚኒስትር አቶ ሃብታሙ ተገኝ እንዳሉት ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ ሀብት ቢኖራትም አውጥታ ግን እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡

 

እያወጣች የምትጠቀምባቸው ውስን የማዕድን ሀብቶችም ቢሆኑ እሴት እየጨመረች ከመላክ ይልቅ በጥሬ እቃ ነው የምትልከው ያሉት ሚንስትሩ ይህ ነገር ከፍተኛ ገቢ እያሳጣ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትርክ ኃይል ስራ አስፈጻሚ  አሸብር ባልቻ(ኢ/ር) በበኩላቸው ሀገሪቱ አሁን ላይ በኃይል አቅርቦት ችግር እየገጠማት ባይሆንም ፍላጎቶች በየጊዜው በዚህ ልክ የሚጨምሩ ከሆነ የከፋ የኃይል እጥረት በቅርቡ ሊያጋጥማት ይችላል ይላሉ፡፡

 

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከወዲሁ የሀይል መስመሮችን ከማደስ ባለፈ በዘርፉ የግል ተቋማት እንዲገቡ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

 

መንግስት ከውጪ የሚመጡ አልሚዎችን እርካሽ የኃይል አቅርቦት አለ እያለ ቢያመጣም መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ ብዙ አልሚዎች ለኪሳራ እየተዳረጉ ነው ሲሉ ኢንጅነር አሸብር ተናግረዋል፡፡

 

ከዚህም ባለፈ ኢንዱስትሪ አካባቢ ያለው የኃይል ታሪፍ ዋጋ ዝቅተኛ ነው ይህንን ለማስተካከል እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ኢንጅነሩ የታሪፍ ማስተካከያው ተግባራዊ ለማድረግ ስራዎች አሁን እየጨረስን ነው ብለዋል፡፡

 

የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ሀብታሙ በበኩላቸው በማዕድን ዘርፍ እሴት ጨምሮ ወደ ውጪ መላኩ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም ቢያንስ በከፊል እሴት ጨምሮ ወደ ገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች አሁን ላይ እየሰራንበት ነው ብለዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ስያሜ እየተካሄደ ያለው የሀገር ውስጥ አምራቾች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽን ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን ጎን ለጎን አምራች ዘርፉን የተሻለ ስራ እንዲሰራ ለማስቻል የሚረዱ ውይይቶች እንደተካሄዱበት ሰምተናል፡፡

 

በረከት አካሉ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

 

Comments


bottom of page