ከተቀመጠው ደረጃ በላይ የካርበን ልቀት ያላቸው መኪኖች እንዳይነዱ የሚያግድ መመሪያ ስራ ላይ ሊውል ነው፡፡
በተሽከርካሪዎች የበካይ ጋዝ ወይም ካርበን ልቀት የሚፈጠርን የአየር ብክለትን ለመቆጣጠር የሚያስችል አስገዳጅ መመሪያ መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡
መመሪያው በአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የተዘጋጀ ነው፡፡
የተዘጋጀው መመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ ሰምተናል፡፡
በከተማዋ ያለው የአየር ብክለት መጠን ከአለም አቀፍ ብሎም እንደ ሀገር ከወጣው ስታንዳርድ ወይም መለኪያ ከማለፉ አኳያ አስገዳጅ መመሪያው እንዲወጣ ምክንያት መሆኑም ተነግሯል፡፡
በከተማዋ ከሚከሰተው የአየር ብክለት ውስጥ 27 በመቶው ከተሽከርካሪዎች የጭስ እና የጋዝ ብናኝ ምክንያት እየተከሰተ መሆኑንም ሰምተናል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ በከተማዋ ያለው የአየር ብክለት አስጊ ደረጃ ላይ በመድረሱ አስገዳጅ መመሪያው አስፈላጊ ሆኖ ስለታመነበት እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በተሽከርካሪዎች ላይ በሚደረግ ፍተሻ ከጭስ እና ከጋዝ ልቀት አልፈው ከተገኙ ለጊዜወ አገልግሎት እንዳይሰጡ ይደረጋሉ ተብሏል፡፡
የአንድ መኪና የካርቦን ሞኖክሳይድ ልቀት በኪሎ ሜትር ከ0 ነጥብ 5 ግራም መብለጥ የለበትም ተብሏልል፡፡
ሆኖም ግን እነኝህን ተሽከርካሪዎች የተሻለ ቴክኖሎጂዎች እንዲገጠምላቸው እና የብክለት መጠኑ እንዲቀንስ አስፈላጊውን የጥገና ስራ እንዲደረግላቸው ይደረጋልም ተብሏል፡፡
መመሪያው በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባም ይጠበቃል፡፡
ፍቅሩ አምባቸው
コメント