የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአማራ ክልል ያለው የሰላም እጦት የምቀበለውን ቅሬታ ከ80 በመቶ በላይ ቀንሶብኛል አለ፡፡
በክልሉ ያለው አለመረጋጋት ተንቀሳቅሶ ለመስራት እንቅፋት ስለሆነብኝ ውስን የሆኑ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ብቻ ለመስራት ተገድጃለሁ ሲል የተቋሙ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለሸገር ተናግሯል፡፡
50 በመቶ የሚሆነውን የክልሉን አካባቢ እንኳን ተደራሽ ማድረግ እንዳልቻለ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አስረድቷል፡፡
ባለፈው አመት በመዝገብ 1 ሺህ 300 በላይ አቤቱታዎች ተቀብለናል ያሉት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሀላፊ ጋሻነው ደሴ ዘንድሮ ግን የተቀበልነው መዝገብ ከ200 አይዘልም ብለዋል፡፡
በክልሉ ያለው የሰላም እጦት ተንቀሳቅሶም ሆነ በስልክ ለመስራት አስቸጋሪ እንደሆነበት የተናገረው የአማራ ክልል የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ይህም የዲሞክራሲ ተቋማት ስራቸውን እንዳይሰሩ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥረዋል ብለዋል፡፡
ቅ/ጽ/ቤቱ በክልሉ ያለው የትጥቅ ትግል በባህር ዳር ዙሪያ በጎንደር እና በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ለመስራት እንዳስገደደው ለሸገር አስረድተዋል፡፡
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከአማራ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ያሉ አለመረጋጋትም ከአዲስ አበባ ከ200 በላይ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ለመስራት መቸገሩን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
Yorumlar