በኢትዮጵያ ያሉት ባንኮች ትርፋማነታቸው፣ ያላቸው ሀብት፣ ካፒታል፣ የቁጠባ መጠን እና በሌሎች አሃዛዊ መረጃዎች እየተጠቀሱላቸው በጥሩ ጎዳና ላይ መሆናቸው ሲነገር ይሰማል፡፡
ለአብነትም የባንኮች ተቀማጭ ከ 2.29 ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
በዚህ ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ከ 124.2 ቢሊየን ብር በላይ አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ባንኮቹ ሰብስበዋል፡፡
አጠቃላይ ባንኮች የሰጡት ብድርም ከሁለት ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው እና የባንኮችን ሁኔታ በሚያስረዳው ሪፖርቱ የሀገሪቱ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር አብዛኛው የተከማቸው በጥቂት ተበዳሪዎች ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡
ሆኖም ግን ባንኩ የሀገሪቱ ባንኮች በአብዛኛዎቹ መለኪያዎች ጤናማ ናቸው ይላል፡፡
ሸገር ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ የባንኮቹን ጤናማነት ከሚሰጡት አገልግሎትና ከደንበኞች እርካታ ጋር እያጣቀሱ የጤናማነታቸው እውነተኝነት ላይ ጥያቄ ያነሱበታል፡፡
ባለሞያው አቶ ያዕቆብ በቀለ የባንኮች የተቀማጭ መጨመር፤ ገንዘብ ከባንክ ውጪ እንደይሆን በመባሉ በግዴታም ጭምር ስለተደረገ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
‘’ብርን እንኳን በቀን ማውጣት የሚቻለው በገደብ ነው፣ ሰው ታሞ አንኳን 20 ሺህ ብር ስጡን ሲባሉ የማይሰጡ ብዙ ብንኮች አሉ’’ ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ሁሉም ባንኮች ብድር የወሰዱ ሰዎች ብዛት 350 ሺህ አካባቢ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ እንደሰፈረውም የባንክ ብድሮች በጥቂት ተበዳሪዎች ጋር ተከማችቷል፡፡
ሪፖርቱ ላይ እንደተቀሰው ሁሉም ባንኮች እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ድረስ ከሰጡት 1.9 ትሪሊዮን ብር ብድር ውስጥ 23.5 በመቶውን ያበደሩት ለአስር ተበዳሪዎ ብቻ ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ባንኮች ደግሞ ለሀላፊዎቻቸው የሚሰጡትን ብድር ጤናማነት አቶ ያዕቆብ ይጠይቃሉ፡፡
ንጋቱ ሙሉ
Comments