top of page

ግንቦት 30፣2016 - በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ታስረው የቆዩ ፖለቲከኞችም ይሁኑ ሌሎች፤ አዋጁ ስለተጠናቀቀ ሊፈቱ ይገባል ሲል የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ተናገረ

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ታስረው የቆዩ ፖለቲከኞችም ይሁኑ ሌሎች፤ አዋጁ ስለተጠናቀቀ ሊፈቱ ይገባል ሲል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተናገረ፡፡

 

ለ10 ወራት በአማራ ክልል እና እንዳስፈላጊነቱ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ተግባራዊ እንዲደረግ ተጥሎ  የቆየው #የአስቸኳይ_ጊዜ_አዋጅ  በትናንትናው እለት ቀነ ገደቡ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡

 

ይህን ተከትሎ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች እንዲፈቱ የጋራ ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡

 

የምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ‘’በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ታስረው የቆዩ ሰዎች የተወሰኑት መለቀቃቸውን ሰምተናል የቀሩትም እንዲፈቱ እንፈልጋለን’’ ብለዋል፡፡

  

በዚሁ ሰሞን 19 እስረኞች እንደተፈቱ እና ከ 20 በለይ የሚሆኑ ደግሞ ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ሰምተናል፤ ይህም የጋራ ምክር ቤቱ የሚደግፈው ተግባር ነው ሲሉ ዋና ሰብሳቢው ነግረውናል፡፡

 

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ያሉ ዜጎችን የሚወክሉ ናቸው ያሉት አቶ ደስታ ዲንቃ ስለዚህ የዜጎች ሁሉ አያያዝ በህግ እና በህግ ብቻ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

 

ፖለቲከኞችን፣ የፖለቲካ አመራሮችም፣ ደጋፊዎችም፣ አባላትም ያለአግባብ ታስረዉ መንገላታት የለባቸዉም፤ ዜጎችን ማንገላታት በራሱ የችግር መፍጠሪያ መንገድ እንጂ መፍትሄ አይሆንም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

 

አሁን ወደ ምክክር እና ንግግር ነው መሄድ ያለብን ብለዋል ዋና ሰብሳቢው፡፡

 

‘’ባለፈው ከምክትል ጠቅላይ ሚስትሩ ጋር በነበረን ውይይትም ይህን አንስተናል ሁሉም ሥርዓትን መያዝ እንዳለበት ተነጋግረናል፤ ሁሉም አካሄድ ህግን የተከተለ እንዲሆንም በተደጋጋሚ እየተከታተልን ነው’’ ሲሉ አቶ ደስታ ዲንቃ አብራርተዋል፡፡


 

ያሬድ እንዳሻው



Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page