top of page

ግንቦት 29፣2016 - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዬን እንዳላቀርብ ተደርጌያለሁ አለች

  • sheger1021fm
  • Jun 6, 2024
  • 1 min read

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዬን እንዳላቀርብ ተደርጌያለሁ አለች፡፡


በአጀንዳ ልየታው ቤተ እምነቶች ሊመከርባቸው ይገባል ያሉት ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጀንዳዬን እንዳላቀርብ ተደርጊያለሁ ስትል ቅሬታዋን አቅርባለች፡፡


ቤተ ክርስቲያኗ ይህንን ያለችው የግንቦት 2016 ዓ/ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ማጠቃለያን አስመልክቶ በሰጠችው መግለጫ ነው።


መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ‘’ቤተክርስቲያኗ ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆና ሳለ በሃገራዊ ምክክሩ የተሳትፎ ጥሪ እስከአሁን ድረስ በይፋ አልቀረበላትም በዚህም ቅር ተሰኝተናል’’ ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ቤተክርሲያኗ አጀንዳዋን አላቀረበችም፣ በመሆኑም ቤተ-ክርስቲያኗ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ተናግረዋል።


የቤተ ክርስቲያኗን ቅሬታ ተከትሎ ሸገር የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ጠይቋል፤ ኮሚሽኑ በጉዳዩ ዙሪያ መክሬበት ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል፡፡


በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በተካሄደው አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊ ከሆኑትና አጀንዳዎቻቸውንም ለኮሚሽኑ ካስገቡ የሃይማኖት ተቋማት መካካል ሸገር የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባኤን አነጋግሯል፡፡


ጉባኤው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የቁጥራቸውንና የአስተዋፅኦዋቸውን ያህል በታሪክም ይሁን በፖለቲካው አልተወከሉም፤ በእምነታቸው ምክንያት መገለል ደርሶባቸዋል ብሎ ያምናል ያሉን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባኤን ወክለው የተገኙት የታሪክ ተመራማሪው አቶ ሰኢድ መሃመድ ናቸው፡፡


እነዚህም ጉዳዮች ምክክር እንዲደረግባቸው ለኮሚሽኑ በአጀንዳነት አስይዘናልም ብለዋል፡፡


የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን በመወከል የተገኙት አቶ አደም ተሾመ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት እኩልነት በተግባር ይኑር የሚለው ጉዳይ እንዲሁም ሁሉንም ሃማኖቶች የሚያስማሙ ብሄራዊ ጀግኖች፣ ምልክቶች፣ ታሪክና ትርክቶች ይኑሩ የሚሉት ጉዳዮች መነሳታቸውን ነግረውናል፡፡


በሂደቱ በየእምነት ተቋማት የሚነሱ አብዛኞቹ ችግሮች ተነስተው ለዋናው ሃገራዊ ምክክር በአጀንዳነት ተይዘዋልም ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የሚያሰባሰብበትን የአዲስ አበባውን መድረክ ቢያጠናቅቅም አሁንም ድረስ አጀንዳዎችንና ቅሬታዎችን መቀበሌን እቀጥላለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡


ምታምር ፀጋው



Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page