#በሀገራዊ ምክክር የመምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ እና የመንግስት ሰራተኞች ተወካዮች አጀንዳ እና ስጋት ምንድነው?
በአዲስ አበባ ለሰባት ቀናት በተካሄደው እና በላፈው ማክሰኞ እለት በተጠናቀቀው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የመምህራን፣ መንግስት ሰራተኞች እና የንግዱ ማህበረሰብ ስጋት እና ጥያቄዎቻቸውን ለሸገር ነግረዋል፡፡
#የመምህራን ማህበር ተወካዮች፤ መምህራን ለሚሰጡትን አገልግሎት ሚመጥን ክፍያ እንዲከፈላቸው፣ የቤት እና ሌሎችም ችግሮች አንዲፈቱላቸው፤ ይህ ከሆነም ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ደርሻ አንደሚኖረው አጀንዳቸው አድርገው አቅርበዋል፡፡
በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥም ጠይቀዋል፡፡
ያቀረቧቸው አጀንዳዎች ለምክክር ጉባዔ ቀርበው መፍትሄ ካላገኙ በከተማዋ ያሉ ከ30 ሺህ በላይ የመምህራን ጥያቄ ተዳፍኖ እንዳይቀር ስጋት አለን ብለዋል፡፡
#በሀገሪቱ ሰላም እና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ፍትሀዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ፣የሚሰራው ስራ እና የሚከፈለው ክፍያ ማመጣጠን ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች ተወካዮች አጀንዳ እንዲሆኑ ካስገቧቸው መካከል ናቸው፡፡
ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈለው የመንግስት ሰራተኛ ነው ያሉት ተወካዮቹ፤ ሰራተኛው የሚከፍለው ግብርም እንዲስተካካል እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ጥያቄዎቹ ቀላል ናቸው ተብለው ለምክክር ጉባዔ ሳይቀርቡ ከቀሩ ሰራተኛው በችግር ውስጥ እንዳይቀጥል ስጋት አለን ብለዋል የመንግስት ሰራተኞች ተወካዮቹ፡፡
#ከክልሎችም ሆነ በከተሞች አስተዳደር በሚደርስበት መፈናቀል የካሳ ክፍያ እንዲከፈለው፣ ተለዋጭ የማምቻ እና መስሪያ ቦታ እንዲሰጠዉ በአጃንዳነት አስይዘናል ሲሉ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ነግረውናል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ስጋት ደግሞ፤ ኮሚሽኑ ይህን ያህል አጀንዳ ብቻ ነው የምፈልገው እነዚህን ጥያቄዎች በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች መመለስ የሚችሉ ናቸው ተብለው እንዳይጣ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
#የሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን ምላሽ
ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) ስጋቶቹ ትክክለኛ መሆናቸው አስረድተው፤ ብዙ አጀንዳዎች እደመነሳታቸው መጠን ብዙም ፍላጎቶች አሉ ብለዋል፡፡
‘’የኔ አጀንዳ እንዳይቀር ብሎ መስጋት ጤነኛ ስጋት እና መስተናገድ አለበት ብዬ አስባለዉ’’ ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በአዋጁ መሰረት፤ የምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት፤ አጀንዳዎችን ሰብስቦ መቅረት የሌለበት የቱ ነዉ የሚለውን እንደሚቀርፅ ኮሚሽነር አምባዬ ጠቁመዋል፡፡
በመቀጠልም፤ ሌሎችን ባለድርሻ አካላት አካቶ መጨረሻ እነዚህ ሃሳቦች መቅረብ አለባቸው የሚለውን ለይቶ ለህዝብ ያቀርባል፤ በዚህ ሂደት ካለፍን ስጋቶቹን እንፈታለን ብለን እናስባለን ሲሉም ነግረዉናል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comments