top of page

ግንቦት 28 2017 - የ2018 በጀት 2 ትሪሊየን ብር የተጠጋ እንዲሆን የቀረበው ረቂቅ፣ ወደ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመራ

  • sheger1021fm
  • Jun 5
  • 1 min read

የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ በጀት ሁለት ትሪሊየን ብር የተጠጋ እንዲሆን የቀረበው ረቂቅ፣ ለውሳኔ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራ።


የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ተወያይቶ ተጨማሪ ሀሳብ በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡


47ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 47ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።


ምክር ቤቱ በቅድሚያ የ2018 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ መወያየቱ ተወርቷል።


የ2018 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት በጀት በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም፤ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ በተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መርዳትን ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀቱ ተነግሯል።

የ2018-2022 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍን እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸምን በመገምገም የበጀት ረቂቁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ተብሏል።


በዚሁ መሠረትም ለፌዴራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ወደ ሁለት ትሪሊዮን የሚጠጋ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡


ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግስት የ2018 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ተጨማሪ ሀሳብ በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል ተብሏል።


ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው በጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች(በስታርታፕ)ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶም ውሳኔ አሳልፏል።


ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎች (ስታርታፖች) የሚመሰረቱበት፣ የሚንቀሳቀሱበትና የሚያድጉበት እንዲሁም ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ አዳዲስ ምርቶችን የሚያመርቱበትና አገልግሎቶችን የሚሰጡበት፣ በዘርፉም ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እንዲያስችል ሆኖ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ተብሏል።


የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ በአዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page