top of page

ግንቦት 28 2017 - የገበያ ቅኝት - የእንቁላል ዋጋ መናር

  • sheger1021fm
  • Jun 5
  • 2 min read

የእንቁላል ዋጋ ከሶስት ወራት በፊት ከነበረው በእጥፍ ጨምሯል፡፡


በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ የእንቁላል አምራቾች ከስራው በብዛት መውጣታቸውንም ሰምተናል፡፡


ለዋጋው መወደድ ዋንኛው ምክንያት የምርት እጥረት ነው፤እጥረቱም የመጣው በርካታ የዶሮ አርቢዎች በኪሳራ ከስራው በመውጣታቸው እንደሆነ የዶሮ አምራቾችና አቀናባሪዎች ማህበር ነግሮናል፡፡


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሚታይበትን የእንቁላል ዋጋን በከተማዋ ባሉ ከሾላ ገበያ ጀምሮ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውረን ጠይቀናል፡፡


በቅኝታችን በጀሞ፣ቄራ፣ፒያሳና ሾላ አካባቢ ያሉ ገበያዎችን ተመልክተናል፡፡


በዚህም መሰረት በጀሞና ቲያሳ አካባቢ አንድ እንቁላል የሃበሻው እስከ 23 ብር የፈረንጁ እስከ 21 ብር ይሸጣል፤በቄራ ገበያ አከፋፋዮች የሃበሻውን እንቁላል 21ብር፣የፈረንጁን 20 ብር እየሸጡ ነው፡፡


በሾላ ገበያ ግን የተወሰነ የዋጋ መቀነስ እንዳለ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ገበያ ሁለቱም አይነት እንቁላል በ20 ብር ይሸጣል፡፡

ያነጋገርናቸው ነጋዴዎችም የእንቁላል ዋጋ ከወትሮው በተለየ ዋጋው እንዲጨምር ምክንያቱ የምርት እጥረት ነው፤ከገበያው የሚፈልገው ያህል መጠን እየቀረበ አይደለም ይላሉ፡፡


በዚህም ምክንያት አንዳንድ ነጋዴዎች ከገበያው እየወጡ መሆኑንም ነግረውናል፡፡


የእንቁላል ዋጋ እንዲህ አልቀመስ ከማለቱ በፊት በተለይ ከ3 ወራት በፊት እስከ 10 እና 12 ብር ሲሸጡ እንደነበር የሚያስታውሱት ነጋዴዎቹ፤በአጭር ጊዜ ውስጥ ዋጋው በእጥፍ ቢጨምርም ከዚህ በኋላ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚጀመሩ አጿማት ፍላጎቱን ሊቀንሱት ስለሚችሉ ዋጋው ሊቀንስ ይችላል የሚል ግምት አላቸው፡፡


በሌላ በኩል የእንቁላል ዋጋ ንረት ከአቅም በላይ እየሆነ ነው ያሉን ያነጋገርናቸው ሸማቾች የሚገዙትን መጠን ለመቀነስ እንደተገደዱ እንዲሁም የዋጋው ውድነት በዚሁ ከቀጠለ ለህፃናት ልጆቻችን እንቁላል መመገብ ለማቆም እንገደዳለን ብለውናል፡፡


ስለ ጉዳዩ የጠየቅነው የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማህበር በበኩሉ እርግጥ ነው የእንቁላል ዋጋ በጣም ጨምሯል፡፡


ለዚህ መነሻ ምክንያቱ የምርት እጥረት በመፈጠሩ ነው ብሎናል፡፡


የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ፀሃይነህ እንደነገሩን ባለፈው ዓመት የተትረፈረፈ የእንቁላል ምርት ነበር፤ይሁንና ገበያ ባለመኖሩ አምራቹ ከ10 ብር ጀምሮ ሲሸጥ የነበረው ካመረተበት ዋጋ ቀንሶ ነበር፤ ይህ በመሆኑ ብዙዎች ከስረው ከገበያው ወጥተዋል፡፡


በዘንድሮ ዓመት የምርት እጥረት የተፈጠረው አምራች ባለመኖሩ ነው የሚሉት አቶ ዝናው ይህ ችግር እንዲቅረፍ የእንቁላል ኤክስፖርት እንዲፈቀድ መንግስትን ጠይቀን፤ ዘንድሮ ተፈቅዷልም ብለዋል፡፡


ሌላው ለዋጋው መናር ምክንያቱ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በመኖ እና በእንቁላል ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ በመጣሉ እንደሆነም ያነሳሉ፤ይህም ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ ከመንግስት አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለውናል፡፡


ከመደበኛ ገበያው ከ15 እስከ 20 በመቶ በቀነሰ ዋጋ ምርቶች ለሸማቹ እንዲቀርቡ እያደረገ እንደሆነ የሚናገረው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን በቅዳሜና እሁድ ገበያ እንቁላልን በምን ያህል ዋጋ እያቀረባችሁ ነው ስንል ጠይቀናል፡፡


ከቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ከአቶ አሸናፊ ብርሃኑ እንደሰማነው የእንቁላል ምርት እጥረት ስላለ እንደተባለው በቀነሰ ዋጋ ሳይሆን በየሱቁ በሚሸጥበት ዋጋ በ22 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page