ግንቦት 28 2017 - ''ኢትዮጵያ የካሳ ኮሚሽን የወሰነላትን ገንዘብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስመለስ የምታደረገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች'' ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር)
- sheger1021fm
- Jun 5
- 2 min read
ኢትዮጵያ የካሳ ኮሚሽን የወሰነላትን ገንዘብ ጨምሮ ሌሎች ተሰብሳቢ ገንዘቧን፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስመለስ የምታደረገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ከየትኛው ጎረቤት ሀገር አንደሆነ ግን በስም አልጠቀሱም፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) ይህን የተናገሩት ዛሬ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
የህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት አባል የሆኑት አቶ እሸቱ ገ/ማርያም ‘’የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ ይበርር ነበር፣ እሁን ግን እንደተቋረጠ እየሰማን ነው፣ የአየር መንገዱ ሃብትም ጨምር እንደተወሰደ ይነገራል ይሄንን በዲፕሎማሲ እንዲፈታ ምን አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ ማብራሪያ ቢሰጠን?’’ ሲሉ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ‘’የአለም አቀፍ አቪዬሽን ድርጅት የሚያወጣው ደረጃ አለው፣ በዚህም የተለያዩ የአየር መንገዶችን ሃብት አፍነው ይዘው አላስወጣ ያሉ አገራት እነማን ናቸወ ብሎ በዓመቱ በሚያወጣወ ሪፖርት ውስጥ በቀዳሚነት የሚሰለፉት አንዳንድ ጎረቤቶቻችን ናቸው’’ ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ‘’እንዚህ ጎረቤቶቻችን ብዙ የአውሮፕላን ምልልስ እና እንቅስቃሴ ያለባቸው አይደሉም፣ አዲስ አበባ በቀን የሚኖረው እነሱ ጋር ምናልባት በወር ቢኖር ነው፣ ገንዘብ በመያዝ ግን ቁጥር አንድ ደረጃ ላይ የሚሰለፉ ናቸው’’ ብለው በስም ያለጠቀሱትን አገር ወቅሰዋል፡፡

‘’ይህን ጉዳይ የሚከታተል አለም አቀፍ ድርጅት እና ስምምነት አለ’’ ያሉት ሚኒስትሩ ነገር ግን በስም ያልጠቀሱት እና ጎረቤት ሲሉ የጠቀሱት አገር ያለው መንግስት ጋር ይህን ‘’አክብሮ የመስራት ጉድለት አለበት’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‘’እኛ ግን በእነዚህ ተቋማት እና አሰራሮች መሰረት ንበረታችንና ገንዘባችንን ለማስመለስ የምናደርገውን ጥረት እንቀጥላለን’’ ብለዋል፡፡
ያለን ሃቅ እና ንብረት ይህ ብቻ አይደለም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) ሃሳባችን የአየር መንገዱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሚጠቀሱ ተሰብሳቢ ሂሳቦች አሉን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‘’እንደሚታወቀው የካሳ ኮሚሽን ነበረ፣ የካሳ ኮሚሽኑ የወሰነልን ገንዘብም አለ’’ ብለዋል፡፡ በሆደ ሰፊነት እስከ ዛሬ ያልተሰበሰበ በገንዘብ የሚገለጹም፣ በገንዘብ የማይገለጹም ሊኖር ይችሉ ይሆናል በሂደት ይታያል’’ ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
እኛ በሰላማዊ በፖለቲካዊ እና ህጋዊ አግባብ ንብረታችንንና ጥቅማችንን ለማስከበር የምናደርገውን እንቅስቃሴ እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments