በፊሊፒንስ ኔግሮስ ደሴት እሳተ ገሞራ ፈነዳ፡፡
እሳተ ገሞራው የፈነዳው በካንሎን ተራራ እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
እሳተ ገሞራው እንደፈነዳ በአቅራቢያው ይኖሩ የነበሩ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአደጋ ወደሚጠበቁበት ስፍራ ተዛውረዋል ተብሏል፡፡
ፍንዳታው ታላቅ ነበር ተብሏል፡፡
እሳተ ገሞራው ትፍ አመድ፣ እሳት እና ፉል ውሃ እየረጨ መሆኑ ታውቋል፡፡
ፖሊስ በ4 ኪሎ ሜትር መጠነ ዙሪያ ወደ እሳተ ገሞራው ስፍራ እንዳይታለፍ መከልከሉ ተጠቅሷል፡፡
በፍንዳታው ወቅት እሳተ ገሞራው በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ታውቋል፡፡
በቱርክ በልምምድ ላይ የነበረች አውሮፕላን በመከስከሷ የ2 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ፡፡
አደጋ የገጠማት የመለማመጃ አውሮፕላን የአገሪቱ አየር ሀይል ንብረት መሆኗን የመከላከያ ሹሞች እንደተናገሩ TRT ፅፏል፡፡
አውሮፕላኗ በምን ምክንያት ልትከሰከሰች እንደቻለች ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡
ምርመራ መካሄዱ አይቀርም ተብሏል፡፡
የአውሮፕላኗን ስብርባሪ ለማግኘት ፍለጋው መቀጠሉ ታውቋል፡፡
በሕንድ ጠቅላላ ምርጫ (NDA) የተሰኘው የነጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የፖለቲካ ጥምረት ማሸነፉ ተሰማ፡፡
BJP የተሰኘው የፖለቲካ ማህበር አውራው የሆነበት NDA የፖለቲካ ጥምረት 543 መቀመጫዎች ባሉት ፓርላማ 290 ወንበሮችን በማግኘት ማሸነፉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ምርጫው በ7 ምዕራፎች ተከፋፍሎ ለ6 ሳምንታት ተካሂዶ መጠቃለሉ ታውቋል፡፡
1 ቢሊዮን ያህል ድምፅ ሰጭዎች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን፤ ከ66 በመቶ ያላነሱት ድምፅ የሰጡበት ነው ተብሏል፡፡
NDA የተሰኘው የእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጥምረት በፓርላማው እስከ 400 መቀመጫዎችን ለማሸነፍ አልሞ ነበር፡፡
በ290 መቀመጫዎች ጠባብ አብላጫነቱን ቢይዝም ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ውጤቱን ታሪካዊ ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ሕንድ በምርጫዋ የህዝብ ተሳትፎ ታላቅነት የአለማችን ትልቋ ዲሞክራሲ ተሰኝታ እንደምትታወቅ ዘገባው አስታውሷል፡፡
በናይጀርያ ተጀምሮ የነበረው የስራ ማቆም አድማ እንዲገታ ተደረገ፡፡
በሁለት የሰራተኞች ማህበራት ህብረቶች ተጀምሮ የነበረው አድማ ናይጀሪያን ክፉኛ አሽመድምዷት እንደነበር TRT አስታውሷል፡፡
አድማው የተጠራው በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ለሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግ በመጠየቅ ነበር፡፡
በአድማው በናይጀሪያ ብዙ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መቋረጥ አስከትሎ እንደነበር በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ታላላቅ ኤርፖርቶችንም ከአገልግሎት ውጭ አድርጓቸው ነበር፡፡
የሰራተኞች ማህበራት ህብረቶቹ አድማውን ትተነዋል ያሉት መንግስት በጉዳዩ ላይ መነጋገር እሻለሁ ማለቱን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
የእስራኤሉ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ኤታማር ቤን ግቪር የሊባኖሱን ሔዝቦላህ ድምጥማጡን እናጥፋው አሉ፡፡
ቤን ግቪር በእስራኤል መንግስት ውስጥ ካሉ አክራሪ ፖለቲከኞች አንዱ እንደሆኑ አናዶሉ አስታውሷል፡፡
የእስራኤሉ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ሄዝቦላህን እናጥፋው ያሉት ከሊባኖስ የተተኮሰ ሮኬት በሰሜናዊ እስራኤል የሰደድ እሳት ካስነሳ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
ቤን ግቪር የእስራኤል ጦር ዋነኛ ተግባር ሄዝቦላህን መደምሰስ መሆን እንዳለበት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
የእስራኤል የእሳት አደጋ ተከላካዮች ቃጠሎውን ለመቆጣጠር እየታገሉ ነው ተብሏል፡፡
ደቡባዊ የሊባኖስ ክፍል እና ሰሜናዊ እስራኤል የጋዛው ጦርነት ቅጥያ ተደርጎ እየታየ ነው፡፡
Comments