ግንቦት 27 2017 - የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ስብሰባዎችን እንዳያካሂዱ የሚያደርጉ ውክቢያዎች እና ክልከላዎች እንዲቆሙላቸው ጠየቁ፡፡
- sheger1021fm
- Jun 4, 2025
- 1 min read
የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ስብሰባዎችን፣ ጉባዔዎችን እንዲሁም ሌሎች መድረኮችን እንዳያካሂዱ የሚያደርጉ ውክቢያዎች እና ክልከላዎች እንዲቆሙላቸው ጠየቁ፡፡
ፓርቲዎቹ ይህን የጠየቁት ከአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ባደረጉት ወይይት ላይ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ስራዎችን ስንሰራ አባላትን የማዋከብ ስራ የሚሰሩ የጸጥታ አካላት አሉ የከተማ አስተዳደሩ እሱን ችግር ቢፈታልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ከሆነ ለመንግስት መነጽር ስለሚሆኑ በፓርቲ አባላት ላይ የሚፈጸሙ ውክቢዎች ስለሚታዩ አስተዳደሩ ይህን ቢያይልን ሲሉ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
በወይይቱ ላይ የተሳተፉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተወካይ በበኩላቸው እንደ ድርጅት ልናደርጋቸው የምንፈልጋቸው መድረኮች ለማዘጋጀት ሆቴሎችን ሄደን ስንጠይቅ እንደፈለግነው እና ህጉ በሚፈቅድልን ልክ እያገኘን አይደለም ብለዋል፡፡

ስብሰባዎችን ማካሄድ አልቻልንም የፓርቲውን ብሄራዊ መድረክ ስብሰባ ለማድረግ እንኳን እስከ ዛሬ ተቸግረናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለውም አባሎቻችንን በከተማዋ ውስጥ የማዋከብ እና የማሰር ሁኔታ ጭምር ስላለ እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱልን እንጠይቃለን ብለዋል ተወካዩ፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን መጠናከራቸውን የሚገድቡ ነገሮች ካሉ አንድም ይሁን ሁለት ፓርቲ ይህን መሰል ችግር ሊገጥመው አይገባም፣ ነገር ግን ችግሩ ካለ መረጃዎችን ወስደን የምናርም ይሆናል ብለዋል፡፡
ፓርቲዎች ለመሰባሰብ፣ ለመነጋገር እና የሚያስፈልጓቸውን አባል ለማፍራት የሚያደርጓቸውን ቀስቀሳዎች የሚያደናቅፉ ክልከላዎች እንዳይኖሩ አመራሮቻችን በቂ ግንዛቤ አላቸው ሲሉ ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡
እንደ ፓርቲም ቁጭ ብለን የተነጋገርንበት ጉዳይ ነው ያሉት ከንቲባዋ ቁጭ ብለን አቋም የወሰድንበት ነው ብለዋል፡፡
ነገር ግን በዚህ ሽፋን ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት እና የህግ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ፓርቲዎችም ለአባሎቻቸው በሚገባ ማስተማር እንዳለባቸው ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

የፀጥታ አካሎች ምን ዓይነት ክፍተት አግኝተው ነው አንዳንዶቻችሁ አዋከቡን ያላችሁት? በዚያ ደረጃ ከሆነ ጉዳዩ ማየት ያስፈልጋል ያሉት ከንቲባው ነገር ግን የህግ ማስከበር ጉዳይ እንዳይሆን በዝርዝር መረጃዎቹን ስጡን እና አጣርተን ምላሽ የምንሰጥበት ይሆናል ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il












Comments