ግንቦት 27 2017 ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናገረ።
- sheger1021fm
- Jun 4
- 2 min read
ይህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኢንቨስትመንት ባንክ እንደሚያደርገው በስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ተነግሯል።
የኢንቨስትመንት ባንኩ በይፋ ስራ መጀመሩን የተናገረው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል(ዶ/ር) እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ትናንት ምሽት ባካሄደው የስራ ማስጀመሪያ ስነስርዓት ነው።
ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ 385 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተመሰረተ መሆኑ ተናግሯል፡፡
አብዛኛው ወይም 70 በመቶ አክሲዮንም የወጋገን ባንክ መሆኑን ሰምተናል።
የወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ስራው ምንድነው?
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ብሩታዊት ዳዊት ዋናኛ የኢንቨስትመንት ባንኩ ስራ ማማከር ነው ብለዋል።

ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች ወይንም ሌሎች ድርጅቶች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ መመዝገብ ቢፈልጉ፣ ድርሻውን መሸጥና ሀብት መጨመር ካሰቡ ሰነድ የሚያዘጋጀውም ሆነ ምክር የሚሰጠው የኢንቨስትመንት ባንኩ ነው ብለውናል።
እንዲሁም የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት የምክር አገልግሎት፤ የስነደ ሙዓለ ንዋዮች አውጭና ገዢ የማገናኘት፣ በውክልና የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት ማመቻቸት፤ እንዲሁም በተፈቀደለት ሌሎች ተዛማጅ የካፒታል ገበያ ዘርፎች ዋንኛ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች አከናዋኝ በመሆን እንደሚሰራ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ባንኩ የተቋማት ግዢ እና ጣምራ፣ ካፒታል መልሶ ማዋቀር (ካፒታል ሪስትራክቸሪንግ) አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ብሩታዊት አብዲ አስረድተዋል፡፡
ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ከወጋገን ባንክ በምን ይለያል?
ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ሲቋቋም ወጋገን ባንክ አክሲዮን ወይም ድርሻ ከመያዙ በስተቀር በአደረጃጀት፣ በማኔጅመንት እና በሚከተለው የአሰራር ስርዓት ሙሉ በሙሉ የተለየ እና ራሱን የቻለ ተቋም እንደሆነ ተነግሯል።
ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ድርጅታቸውን ወይም ኩባንያቸው በሰነደ ሙዓለ ገበያ ማስመዝገብ የሚፈልጉ፣ ድርሻ ወይም አክሲዮን መሸጥ ለሚሹ እንዲሁም በገበያው የሚቀር እክሲዮኖችን መግዛት የሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች አብረውት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።
የኢንቨስትመንት ባንኩ ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም የስራ ፈቃድ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም የንግድ አባልነት ምዝገባ በማከናወን ካፒታል ገበያውን መቀላቀሉን አስታውሷል።
ከወጋገን ካፒታል አክሲዮን ማህበር በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ካፒታል አክሲዮን ኢንቨስትመንት ባንክ እንዲያቋቁም ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል።
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments