አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን በሚከውነው ስራ ለመጭዎቹ አምስት ዓመታት 60 ቢሊየን ብር ያስፈልገኛል አለ፡፡
ከመንግስት 25 ቢሊየኑን ለማግኘት እቅድ መያዙን ተናግሯል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ይታወቃል፡፡
በተለይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት መንገዱን ከጀመረ 8 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን እየሄደበት ያለው መንገድ ጥሩ ጅምር ነው ተብሏል፡፡
በተለይም የሽግግር ሂደቱ 2 ዓመት እንደሚፈጅ የሚነገረው የራስ ገዝነት ሂደቱ በቀሪ ጊዜያት፤ ሂደቶች ተጠናቀው ዩኒቨርሲቲው በይፋ እራስ ገዝ መሆን እንደሚችል እርግጠኛ መሆኑን በጉዳዩ ላይ የዩንቨርስቲው ኃላፊዎች ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
የሽግግር ሂደቱን እስከ ሚጠናቀቅ ድረስ የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ሆነው እያገለገሉ ያሉትን ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌን አሁን ላይ ለሽግግር ሂደቱ ችግር የሆነባቸው የፋይናንስ አቅርቦት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን በሚከውነው ስራ ለመጭዎቹ አምስት አመታት 60 ቢሊየን ብር ያስፈልገናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከመንግስት እና እራሱ ዩንቨርስቲው ከሚያመነጨው ገቢ በሚቀጥሉት 5 አመታት 25 ቢሊየኑን ሊያገኝ የሚችለው ይላሉ፡፡
ቀሪ 35 ቢልየን ብር ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመሆን አንድ የቴክኒክ ቡድን አዋቅሮ የሽግግር ሂደቱ እንዲሳካ እየሰራ እንደሆነ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ እሱም ትልቅ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኤምባሲው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ወደፊት ራስ ገዝ ለሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሆን 316 ሺህ ዶላር እርዳታም ማድረጉን ሰምተናል፡፡
ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት ዩንቨርስቲው አሁን ዋንኛ ትኩረቱ እንደ ሀገር የልህቀት ማእከል መሆን ነው ለዚህም አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ላይ ማሻሻያዎች እየተሰራ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይ ናኦሚ ፌሎውስ በበኩላቸው ትምህርት ሚንስቴር የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የዩንቨርስቲዎች እራስ ገዝ ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ መንግስታቸው እንደሚያደንቅ የተናገሩ ሲሆን ድጋፍም እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሽኔ ዩንቨርስቲዎች እራስ ገዝ ለማድረግ በወጣው አዋጅ መሰረት ሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስፈርቱን አያሟሉም ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ወደፊት ወደ ራስ ገዝነት ለሚሸጋገሩት ዩንቨርስቲዎች ልምድ የሚወሰድበት ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ውጭ 9 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እራስ ገዝ ለመሆን የራሳቸው ስራ እየሰሩ መሆኑን የተነገረ ሲሆን ትምህርት ሚንስቴር ባለው አቅም ልክ ድጋፍ እያደረግሁኝ ነው ይላል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የበጀት ጉድለት የሚገኝባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እራስ ገዝ ለመሆን በሚያደርጉት ሂደት ላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸው በሚገባ እንደሚጤንና ጤነኝነቱ እነሚፈተሽ ሰምተናል፡፡
በረከት አካሉ
Comments