top of page

ግንቦት 27፣2016 - መንግስት፤ ከአዋሽ ኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከቱርክ ኩባንያ ጋር እየተካሰሰ ነው ተባለ

መንግስት፤ ከአዋሽ ኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከቱርኩ ያፒ መርከዚ ኩባንያ የተጠየቀው ካሳ ከፍተኛ የሚባል እና እጅግም የተጋነነ ነው ሲል የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ተናገሩ፡፡


‘’ያፒ መርከዚ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን’’ የተባለ የቱርክ ኩባንያ ከአዋሽ ኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክትን እየሰራ እያለ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የበዙ ንብረቶችን ተዘርፌለሁ በማለት ካሳ እንዲከፈለው የኢትዮጵያ መንግስትን መክሰሱ ተነግሯል፡፡


የባቡር መንገዱ ፕሮጀክትን በተለመከተ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር፤ ከህዝብ እንደራሴዎች ዛሬ ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡


ጉዳዩ እኔን በቀጥታ ባይመለከትም ኩባንያው የጠየቀውም ገንዘብ ከፍተኛ የሚባል እና እጅግም የተጋነነ ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ለአንደራሴዎች ምክር ቤት አስረድተዋል፡፡


ኩባንያው ለተዘረፉበትና ለወደሙበት ንብረቶች የጠየቀው ግንዘብ የተጋነነ እና ከፍተኛ ነው ከማለት ዉጪ በመጠን ምን ያህል እንደሆነ ሚኒስትሩ አልጠቀሱም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም፤ የተዘረፉትና የወደሙት ንብረቶች ኩባንያው የጠየቀውን ካሳ ያህል አይደርስም የሚል መከራከሪያ አቅርቦ ክሱ በሂደት ላይ ነው ተብሏል፡፡


ኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የተጀመረው ከ9 ዓመታት በፊት በ2007 ዓ.ም ሲሆን ግንባታውን አስከ ሰሜኑ ጦርነት ድረስ ሲገነባ ቆይቷል፡፡


‘’ያፒ መርከዚ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን’’ በተባለ በቱርክ የሥራ ተቋራጩ እየተሰራ የነበረው የባቡር መስመሩ፤ 392 ኪ.ሜ የሚረዝም እንደሆነ ተነግሮለት ነበረ፡፡


1.7 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በወቅቱ ለግንባታው የተተመነ ገንዘብ ነው፡፡


የኘሮጀክቱ የማማከር ስራም በፈረንሳዩ ‘’ሲስትራ መልቲ ዲ’’ በተባለ አማካሪ ድርጅት ተይዞ እንደነበረ ተነግሯል፡፡

የባቡር ሀዲድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ፤ 10 ጣቢያዎች፣ 10 ኪ.ሜ ርዝመት ያላቸው 12 ዋሻዎች፣ 52 የተለያዩ ርዝመት ያላቸው ድልድዮች፣ 8 የሀይል መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች(ሰብስቴሽንስ)፣ 12 የሬዲዮ ምሰሶዎች እንዲሁም አንድ የጥገና ማእከል የኖሩታል ተብሎ ይጠበቅ እንደነበረ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page